“ሕገ መንግሥቱን” የጣሰው ማነው?

                                                     በጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ፤

Mr. Trump, have you even read the United States Constitution?” Khizr Khan

ይህ ከላይ የተጠቀሰው ብሂል ያስተጋባው እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ከሃምሌ 25 ቀን እስከ ሃምሌ 28 ቀን ፊላደልፍያ በተደረገው የአሜሪካን የዲሞክራቲክ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ነበር። በዚህ ጉባኤ፤ ከተጋበዙት ተናጋሪዎች መካከል፤ ክሂዘር ካን (ካሃን) የተባሉ የሕግ ባለሙያ ከተናገሩት የተወሰደ ነው። ጥያቄውም ለሪፓብሊካን ፓርቲው እጩ ተወዳዳሪ ለነበሩት፤ ለአሁኑ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ “አቶ ትራምፕ፤ ለመሆኑ የአሜሪካንን ሕገ መንግስት አንበበው ያውቃሉ?” ተብሎ የቀረበ ጥያቄ ነበር። 
እኔም ይህንን ጥያቄ መሰረት በማድረግ፤ ዛሬ የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ተጣስ ብለው ተቃውሞ ለሚያሰሙ ኢትዮጵያውያን፤ ለመሆኑ ‘የኢትዮጵያን ፌደራላዊ ዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ሕገ መንግስት አንብበው ያውቃሉ’ የሚለውን ጥያቄ ላነሳላቸው እፈልጋለሁ። በነገሬ ላይ፤ አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሕገ መንግስት፤ ሕዝብ በቅጡ ያልመከረበት እና ሕዝብ ላይ በግድ የተጫነ ነው ተብሎ በተደጋጋሚ ትችት እንደቀረበበት ይሰመርልኝ። ብዙዎቻችን ሕገ መንግሥቱን ባንቀበለውም፤ ስለሕገ መንግስቱ ባዶ ክርክር የሚያቀርቡ ዜጎችን፤ ስህተታቸውን በጭብጥ ለማስረዳት፤ ሃገሪቱ ላለፉት 23 ዓመታት “ስትገዛ” የነበረበት ሕገ መንግስት ምን ይላል፤ ሕገ መንግስቱንስ የጣሰው ማነው? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይሆናል። (ሕገ መንግስቱ የፀደቀው በ1995 አውሮፓ አቆጣጠር ነበር)። 
ስለሕገ መንግስቱ መጣስ የሚነግሩን ሰዎች፤ በቅድምያ ሕገ መንግስቱ ምን እንደሚል ቢገነዘቡና፤ የመከራከርያ ጭብጥ እንዲሆናቸው፤ ተጣሰ የሚሉትን የሕገ መንግስት አንቀጽ ቢጠቅሱልን ለውይይት በተመቸ ነበር። አብዛኞቹ ግን “ሕገ መንግሥት ተጣሰ” ሲባል ሰምተው ከማስተጋባት ባሻገር፤ ሕገ መንግስቱን አንብበውት እንደማያውቁ፤ ካነበቡትም ምንም ያልተረዱት መሆናቸውን በእርግጠኝነት ለመናገር ይቻላል። ላለፉት 23 ዓመታት፤ ስለዜግነት የሚጠቅሰውን አንቀጽ 6፤ ሰለ ሕገ መንግሥት የበላይነት የደነገገውን አንቀጽ 9፤ የመንግስት በሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ እንዳይገባ የሚከለክለውን አንቀጽ 11፤ ስለመንግሥት ተጠያቂነት የሚገልጸውን አንቀጽ 12፤ ስለ ስብዓዊ መብቶች እና ስለ-እስረኛ አያያዝ የሚያወሱትን ከአንቀጽ 14 እስከ 21 ያሉትን ድንጋጌዎች፤ ከአንቀጽ 29 እስከ አንቀጽ 33 የተጠቀሱትን የዲሞክራሲ እና የዜግነት መብቶች፤ እንዲሁም በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 37 እና 38 የተቀመጡት ፍትሕ የማግኘት እና ስለ ነጻ ምርጫ የተደነገጉትን ሕግጋቶች ገዥው ፓርቲ ሲጥስ ቆይቷል። ላለፉት  23 ዓመታት፤ ስለ ሕገ መንግስት ጥሰት ምንም ያላሉ ሰዎች፤ እንደውም ስለ ሕገ መንግሥቱ መጣስ በተለያየ መድረክ ያነሳነውን ሰዎች፤ በጠላትነ የፈረጁ፤ ሕገ መንግስቱ መጣሱን በፃፉ ሰዎች ላይ ሕገ ወጥ እርምጃ በመንግስት ሲወሰድ፤ የሕገ መንግሥቱ መጣስ ምንም ያላሳሰባቸው፤ የገዥው ፓርቲ ባለሥልጣናት፤ አባላትና ደጋፊዎች፤በቅርቡ በሃገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ለመክሰስ ሲሉና ለማጨናገፍ በማሰብ፤ ሕገ መንግሥት ተጥሷል ሲሉ እና ዞር ብለው አይተውት የማያውቁትን “ሕገ መንግሥት” “ሲያውለበልቡ” ስናይ፤ “ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮሃል” የሚለውን የአበው ተረት ያስታውሳል። 
ዛሬ ሕገ መንግስቱ ተጥሷል የሚሉን ዜጎች፤ የተጣሰውን ሕገ መንግስት አንቀጽ ባይጠቅሱልንም፤ ተጥሷል የሚሉት ሕግ፤ኮከብ የለሹ አረንጓዴ ብጫ ቀይ ባንዲራ በተለይ በባሕር ዳር በመውለብለቡ እና፤ ለዶር አብይ ድጋፍ በተወጣባቸው ሰልፎች፤ የኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማርያም ፎቶ እንዲሁም የሞአ አንበሳ አርማ በመያዙ ነው። ይህ ፀሃፍ፤ የኮሎኔል መንግስቱን ፎቶግራፍ በአደባባይ መያዝ በጽኑ ቢቃወምም፤ ፎቶግራፉን የያዙ ሰዎች፤ ፎቶግራፉን ከፍ አድርገው የመያዝ መብት እንዳላቸውም ያምናል። ለመሆኑ ይህ ክስተት ሕገ መንግስት ተጥሷል የሚያሰኝ ነው ወይ? የሚለውን ጥያቄ፤ ይህ ፀሃፊ፤ የሕገ መንግስቱን አንቀጽ በመጥቀስ፤ ጭብጥ በተንተራሰ አመክንዮ መልስ ይሰጥበታል። የኢትዮያን ባንዲራ አስመልክቶ ሕገ መንግሥቱ ላይ የሰፈረው በአንቀጽ 3 የተደነገገው ነው። አንቀጽ 3 የሚለው እንደሚከተለው ነው።
 አንቀጽ 3 – የኢትዮጵያ ስንደቅ ዓላማ
  1. የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሐል ቢጫ ከታች ቀይ ሆኖ በመሐሉ ብሔራዊ ዓርማ ይኖረዋል። ሦስቱም ቀለማት እኩል ሆነው በአግድም ይቀመጣሉ፡፡
     2. ከሰንደቅ ዓላማው ላይ የሚቀመጠው ብሔራዊ ዓርማ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች እና ሃይማኖቶች በእኩልነትና በአንድነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያንጸባርቅ ይሆናል፡፡
  1. የፌዴራሉ አባሎች የየራሳቸው ስንደቅ ዓላማና ዓርማ ሊኖራቸው ይችላል። ዝርዝሩን በየራሳቸው ምክር ቤት ይወስናሉ።” 
አንቀጽ 3፤ እንደሚያመለክተው፤የትኛውም ንዑስ አንቀጽ ላይ፤ ዜጎች በግልም ይሁን ሕዝበ ተይንት ላይ ሌላ ባንዲራ ማውለብለብ የለባቸውም አይልም። የዚህ አንቀጽ ድንጋጌ፤ የኢትዮጵያ ኦፊሳላዊ ባንዲራ መሆኑን ከመግለጽ በስተቀር፤ኮከብ የለሹ ባንዲራ በዜጎች እንዳይውለበለብ የደነገገው ምንም ነገር የለም። ባንዲራውም ሆነ ሕገ መንግስቱ፤ የፀደቀበት ሁኔታ ተገቢ አለመሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ኮከብ የለሹ ባንዲራን በግል ማውለብለብ የሚከለክል ምንም ዓይነት ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌ እንደሌለ በድጋሚ ማስረገጥ እፈልጋለሁ። ከዚህ የተለየ ሕግ አለ የሚሉን ሰዎች ካሉ፤ በጭብጥ ይከራከሩ። እንደውም፤ በሕገ መንግስቱ የተካተተው አንቀጽ 29 ዜጎች በግላቸው የፈለጉትን ባንዲራ የማውለብለብ መብታቸውን፤ የፈለጉትን ምስል እና ፎፍቶግራፍ የመያዝ መብታቸውን ያረጋግጣል። አንቀጽ 29 በሕገ መንግሥቱ እንደሚከተለው ሰፍሯል።
“አንቀጽ 29 – የአመለካከት እና ሀሳብን በነፃ የመያዝና የመግለጽ መብት
  1. ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት ለመያዝ ይችላል፡፡
    2. ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሀሳቡን የመግለጽ ነፃነት አለው። ይህ ነፃነት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሑፍ ወይም በሕትመት፣   በሥነ ጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ፣ ማንኛውንም ዓይነት መረጃና ሀሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት ነፃነቶችን ያካትታል፡፡” (ሰረዝና ድምቀት የተጨመረ)።
ከላይ በግልጽ እንደሚያሳየው፤ ማንኛውም ሰው ያለምንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት መያዝ ይችላል፤ ሲባል፤ የፈለገውን ባንዲራ በማውለብለብ፤ የፈለገውን መፈክር በማሰማት፤ የፈለገውን ፎቶግራፍ ይዞ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በመገኘት፤ እምነቱንና አመለካከቱን የማንፀባረቅ፤ ሕገ መንግስቱ ያረጋገጠው መብት አለው ማለት ነው። ታድያ ሃቁ ይህ ሆኖ ሳለ፤ ሕገ መንግሥት ተጣሰ ብለው አገር ይያዝ የሚሉት ወገኖች፤ ከምን ጭብጥ ተነስተው ነው? ለመሆኑ እራሳቸው አርቅቀው፤ በጉልበታቸው ያፀደቁትን ሕገ መንግስትስ ያውቁታል ወይ? ብዬ ለመጠየቅም እገደዳለሁ።
በጣም የሚያሳዝነው እና የሚያሳፍረው፤ “ሕገ መንግስቱ ተጣሰ” የሚለውን ሃሳብ፤ በተደጋጋሚ አጉልተው የሚያሰሙት በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ፤ ፊደል ቆጠርን፤ የሚሉ ወገኖች ናቸው። በሚኖሩበት በአሜሪካን ሃገር ውስጥ፤ ባንዲራ ማቃጠል እንኳን መብት ነው። ምን ያክል ጊዜ ነው፤ የናዚ ጀርመንን ባንዲራ ያነገቡ እና የሂትለርን ፎቶ የያዙ ሰዎች በአደባባይ ሰልፍ ሲወጡ ያዩት? እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በየካቲት 2015፤ የአውሮፓ ማህበር፤ የናዚ ጀርመን ምልክቶችን፤ በአውሮፓ እንዳይታዩ ለማገድ የቀረበውን ሃሳብ ውድቅ አድርጎታል፤ ይህም የሆነበት ምክንያት፤ ሃሳብን ከመግለጽ ነፃነት ጋር የሚጋጭ በመሆኑ ነው።በእርግጥ፤ አንዳንድ ዜጎችን ያውካሉ ተብለው የሚታሰቡ ምልክቶችም ሆኑ ሃሳቦች፤ በሕግ ሊታገዱ ይችላሉ። ለምሳሌ በአውስትርያ፤ በአይሁዶች ላይ በናዚ ጀርመን የተፈፀመውን በደል እና ግፍ መካድ በሕግ ያስቀጣል። የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት አንቀጽ 29፤ ንዑስ አንቀጽ 6፤ አንቀጽ 29 ላይ የተደነገጉ መብቶች ላይ ገደብ ሊጥል የሚችል ሕግ ሊወጣ እንደሚችል ቢገልጽም፤ እስካሁን ድረስ ዜጎች የፈለጋቸውን ባንዲራ እንዳያውለበልቡም ሆነ፤ የኮሎኔል መንግስቱን ፎቶ አደባባይ ይዞ መውጣት የከለከለ ሕግ የለም። አለ የሚሉን ወገኖች ሕጉን ጠቅሰው በጭብጥ ያስረዱን። 
ከዚህ ቀደም ተደጋግሞ እንደተጠቀሰው እና፤ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ፤ በቅርቡ ለፓርላማው እንድገለፁት፤ ገዥው ፓርቲ በተደጋጋሚ ሕገ መንግስቱን ጥሷል። ሌላው ቀርቶ አሁንም በሥልጣን ላይ ያለው ከሕግ ውጭ ነው። ዛሬ ስለ ሕገ መንግስት የሚስብኩን ሰዎች፤ ይህ ሁሉ ፀሃይ የሞቀው ሕገ መንግስታዊ ጥሰት ሲኖር የት ነበሩ ብለን ለመጠየቅም እንገደዳለን። ስለሕገ መንግስት ከመሟገት በፊት፤ ሕገ መንግስቱን ቢያንቡና ምን እንደሚል ቢረዱት፤ ለራሳቸውም ለሃገርም ባለውለታ ይሆናሉ የሚል እምነት አለኝ።

 

Comments are closed, but trackbacks and pingbacks are open.