ምን ማድረግ ይሻላል? (አስራት አብርሃም)

ምን ማድረግ ይሻላል? (አስራት አብርሃም)

እዚህ ሀገር ሁሉም ነገር ችግር የሆነበት ሀገር ነው። በተለይ ስለሀገር ያገባኛል፣ ይመለከታኛል ለሚል፣ ስለገዥዎች ህጸጽ፣ ስለስርዓት ብልሽት የሚገልጥ ሰው ሁሉም ነገር ችግር ይሆንበታል። ማንኛውም መጥፎ ነገር ሁሉ በእርሱ ላይ ይደርሳል። ከስራ መባረር፣ እንግልት፣ ስደት፣ እስራት፣ ሞት ወዘተ. ለሌላው ክፍት የሆነ እድል ለእርሱ ዝግ ይሆናል። ሰፊውን መንገድ ይጠባል። ቀና የነበረው ሁሉ ጠማማ ይሆናል። ሜዳውን አባጣ ጎርባጣ ይሆናል። ብርሃን የነበረው ጨለማ ይሆናል፣ ሁሉም ነገር በእርሱ ላይ እንቅፋት እንዲሆን ይፈረድበታል። ካልገደሉህ ያስሩሃል፣ ካላሰሩህ ያስርቡሃል። የሰው እጅ እንድታይ፣ ከጓደኞችህ በታች እንድትሆን፣ ልጆችህ ባንተ ምክንያት ዋጋ እንዲከፍሉ ያደርጉሃል። ነገር ግን ይህ ሁኔታ ምን ቢመር፣ ምን ቢያሳዝን፣ በዓሉ ግርማ እንዳለው ምን ያህል እምባ እምባ ቢያሰኝ፣ በዓላማ፣ በእምነት ምክንያት የመጣ ነውና ከመቀበል ውጭ አማራጭ የለም። ግን ደግሞ ታሪክም እንዲዘግበው፣ ወገንም እንዲሰማው የሆነውን ሁሉ መግለፅ እፈልጋለሁ። “የህገ መንግሥቱ ፈረሰኞች” የሚል መፅሐፍ ጽፌ ካጠናቀቅኩ ቆየት ብያለሁ፣ ወደ ህትመት ለመውሰድ ችግሮች ነበሩ። የመጀመሪያው ችግር የማሳተሚያ ወጪ ነበር፣ ወዳጆቼ አበደሩኝና እሱ ችግር ታለፈ። ከዚያ ማተሚያ ቤት ሳፈላልግ ብዙዎቹ የፖለቲካ መፅሐፍ ስለሆነ አናትምም አሉኝ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ የህትመቱን ዋጋ ከተለመደው እጥፍ እንዲሆን ያደርጉታል። አንዱማ መፅሐፉ ታትሞ ቢሸጥ ከሚያወጣው ዋጋ ከፍ የሚል ሲነግረኝ፣ ጌታው በወርቅ ቀለም ነው እንዴ የምታትመው ነው ያልኩት። ሌላው ደግሞ ይህ መፅሐፍ የፖለቲካ ባይሆን ወይም ኢህአዴግን የሚያሞግስ ቢሆን ኖሮ አትምልህ ነበር ብሎኛል። ስርዓቱን ማሞገስ ፖለቲካ አይደለም ማለት ነው! ማስፈራሪያና ቅጣት ይዞ አይመጣምና። የሆኖ ሆኖ አንድ ማተሚያ ቤት መፅሐፉን ለማሳተም ተስማምቶ ነበር፣ ውልም ገብቶ ነበር፣ ነገር ግን ከቀናት በኋላ ከሌሎች ሰዎች ጋር ሆኜ መፅሐፉ ሳየው ፖለቲካዊ ይዘት አለው፣ ከአስቸኳይ አዋጁ ጋርም ይጋጫል የሚል ምክንያት ሰጥቶኝ ውሉን አፈረሰ፣ ለማሳተም የተቀበለውን ገንዘብ በቼክ መለሰልኝ። እንግዲህ እርሱም አይፈረድበትም፣ ፈርቶ ሊሆን ይችላል። አንድ እውነት ግን አለ፣ ይህ መፅሐፍ ከአስቸኳይ አዋጁ ጋር የሚጋጭ ነገር የለውም፣ መቼም ይህ መፅሐፍ አንድ ቀን መታተሙ አይቀርምና ይዘቱን አንባቢ አይቶ የሚፈርደው ነው የሚሆነው። ሕገ መንግሥቱ በግልጽ ሳንሱር ቀርተዋል ይላል፣ ፈረሰኞቹ ደግሞ በጎን እየሄዱ መተሚያ ቤቶቹ እንደዚያ ያለመፅሐፍ እንዳታሳትሙ እያሉ ያስፈራራቸዋል፣ የእኛ ሰው ደግሞ መብቱን ሰጥቶ በሰላም መኖር ነውና የሚፈልገው የተባለውን ሁሉ እሺ ብሎ ያደርጋል። ይህን ጊዜ መቼም ማለፉ አይቀርም፣ ታሪክ ቦታ ቦታችንን ይሰጠን ይሆናል። ብዙዎች በሚደረገው ትግል ዋጋ ለመክፈል እስካልፈቀዱ ድረስ እንደ ህዝብ እንደ ሀገር እንዴት ነው ነፃ ልንወጣ የምንችለው?! በዚህ ሀገር ጥቃትም እንደደህና ነገር ይደገማል! ከአሁን በፊትም “ከሀገር በስተጀርባ” የተባለው መፅሐፌ ለማሳተም ብዙ መከራ ነበር ያየሁት። ሀገር ቤት እንዳይታተም እክል ገጥሞት የቁርጥ ቀን ወዳጆቼ በሆኑት አቶ ነጋሲ በየነ እና አቶ አብርሃ በላይ አማካኝነት ነበር በአሜሪካን ሀገር ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው። በኋላ የመፅሐፉን መታተም እንዳላስቀሩት ሲረዱ ሀገር ቤትም የመታተም እድል አገኘ። በወቅቱ ስለ እንደዚህ ዓይነት ነገር ብዙ ልምድ ስላልነበረኝ በጣም ደንግጬ ነበር። አሁን ግን ብዙ ባዝንም አልደነገጥኩም። ከዚህ በላይ እንደሚያደርጉ አውቃለሁና። ሀብታሙ አያሌውን በነፍስ ተይዞ ያልራሩ ሰዎች ሌላም ነገር ቢያደርጉ አይገርመኝም። አሁን ጥያቄው፣ እሺ ከስርዓቱ ጋር የአቋም ልዩነት ያለን ሰዎች እንዴት እንኑር፣ በየዩኒቨርስቲው ፖለቲከኛ አትቅጠሩ የተባለ ይመስል፣ ስራ ሳመለክት አይቀጥሩኝም፣ በመጀመሪያ ድግሬ እኮ ኮሌጅ አስተምር ነበር፣ ሁለተኛ ዲግሪ ይዤ ስራ ማጣት ነበረብኝ። የሚገርመው ነገር በኢትዮጵያ ያሉት ሁሉም የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች እኔ በተመረቁበት የፍልስፍና ዘርፍ አስተማሪ ይፈልጋሉ፣ ሎጂክ፣ ሲቪክ፣ ፖለቲካል ፊሎሶፊ፣ ወዘተ “common course” መልክ ለሶሻል ሳይንስ ተማሪዎች ስለሚሰጥ ነው። ግን እነርሱ የማይፈልጉት ሰው ለመቅጠር ፍቃደኛ ስላልሆኑ፣ ክፍት ሆነው እንዲቆዩ ነው የተደረገው ወይም በሌሎች ፊልዶች በተማሩ ነው የሚሸፈኑት፣ በየጊዜው ማስታወቂያ ያወጣሉ፣ ስታመለክት ደግሞ አይቀጥሩም። ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው በመንግስት ደረጃ ቂም ስለተያዘብኝ ነው። መፅሐፍ ፅፈህ እንዳታሳትም ደግሞ አሳታሚዎች ያስፈራራሉ፣ አታሚዎች ያስፈራራሉ፣ መፅሐፍ አከፋፋዮች ያስፈራራሉ፣ መፅሐፍ አዟሪዎች ያስፈራራሉ፣ መፅሐፍ ይቀማሉ፣ ያስራሉ። እሺ እንዴት እንኑር?! እንግዲህ እኔ ከዚህ በኋላ እንዲህ ሆኜ መኖር አልችልም፣ እግሬን ወደ መራኝ እሄዳለሁኝ እንጂ። እነርሱ ሀፍረት የሚባል ነገር አያውቁምና እንደተመለደው ደግሞ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ጠብቀው የትም አትሄድም ብለው ያስቀሩኝ ይሆናል። ከዚህ በኋላ በዚህ ስርዓት ስር መኖር በቃኝ! የትም ቢሆን ሄጄ እኖራለሁኝ! መቼም በአንድ ሀገር እንዲህ ሆነህ እየተሰቃየህ ኑር የሚል ህግ የለም።

2 CommentsComments are closed, but trackbacks and pingbacks are open.