የ1993 (1986 በኢትዮጵያ) የሰላም እና የእርቅ ጉባኤ እንደ አርአያ “ሞዴል”፤

                                                               ከጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ፤

በኢትዮጵያ ላይ አጥሎ የነበረው፤ የጨለማው ጉም መገፈፈ ጀምሮ፤ ሕዝባችን ብሩህ የሆነውን፤ ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ ሥልተ ሥርዓት ለመገንባት፤ ተስፋውን ሰንቆ መንገድ ጀምሯል። ይህ፤ ከ40 ዓመታት በላይ የተደከመበት እና የሚሊዮኖች የሕይወት መስዋዕትነት የተገበረበት ጉዞ ከግቡ እንዲደርስ ብቻ ሳይሆን ከትውልድ ትውልድ ሊተላለፍ የሚችል ቋሚ ስልተ ሥርዓት እንዲሆን፤ ከአሁኑ ጠንካራ መሰረቶችን መጣል ያስፈልጋል። አንድ ቤት ቋሚ ሊሆን የሚችለው በሚያምር ጣራ ስለተብረቀረቀ፤ ወይም ቀልብን በሚስብ ቀለም ስለተቀባ አይደለም። ቤቱን ጠንካራ እና ቋሚ የሚያደርገው የሚገነባበት መሰረት እና፤ ጣራውን አቅፎና ደግፎ የሚይዘው ብርቱ ምሶሶ ነው።

ምንም እንኳን፤ አብዛኛውን ሕዝብ ያስደሰተ እና ለሚሊዮኖች ተስፋ የሰጠ ወቅት ላይ ብንደርስም፤ ብዙ የሚቀረን፤ ገና ያልዳሰስናቸው ችግሮች አሉብን።በተለይም ላለፉት 27 ዓመታት ሕዝባችን እርስ በእርሱ እንዲናከስ፤ የተተከለለተ የዘር ፖለቲካ የጥላቻ ችግኘና አረሙ ከስር መሰረቱ ተነቅሎ እንዲጣል ማድረግ ጊዜ የማይጠይቅ እና፤ ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ ነው።

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፤ “የሕዳሴ አብዮት” ብሎ የከተበው እና፤ በመጣጥፎቹ ለማስተማር የደከመበት የሕዳሴ አብዮት ዘላቂ ሊሆን የሚችለው፤ በሃገራችን ብሄራዊ እርቅ ሲሰፍን ብቻ ነው ብዬ አምናለሁ። በተለይ ላለፉት 27 ዓመታት፤ ብሔራዊ እርቅን አጀንዳ አድርገን በየአቅጣጫው እና ባለን አቅም ሁሉ ስንጮሕ የነበረን፤ ይህ ብሄራዊ እርቅ እውን እንዲሆን አሁንም ተግተን መስራት አለብን። የብሔራዊ እርቅ አጀንዳ በተለይም ውጭ በሚኖረው የተቃዋሚ ሃይል በጽኑ ሲሰራበት የነበረ ቢሆንም፤ የኢሕአዲግ መራሹ መንግሥት በጎ ምላሽ ከመስጠትና፤ የዚህ አጀንዳ መሪ ተዋናይ በመሆን፤ ሃገራችን ብሔራዊ እርቅ እንዲኖር ከማድረግ ይልቅ፤ “ማን ተጣላና ነው፤ የሚታረቀው” በሚል ግብዝ ፈሊጥ፤ ለብሔራዊ እርቅ የሚደረግውን ጥረት በማጥላላትና በማጠልሸት፤ ለብሔራዊ እርቅ የሚሰሩ ዜጎችን በማሰር እና በማጎሳቆል ሕዝባችንን ከፍተኛ አደጋ ላይ ጥሏል።

በተለይ በኦሮም እና በአማራ ክልል በተቀጣጠለው የሕዳሴ አብዮት፤ የእርስ በእርስ ግጭቱ ወደ ዘር ጦርነት ዘልቆ ሊሄድ ይችላላ ከሚል ሥጋት፤ በተለይ ላለፉት ሁለት ዓመታት፤ ብዙዎች ለብሄራዊ እርቅ ደውል ሲደውሉ ቆይተዋል። ገዥው ፓርቲ ከመጣበት ውጥረት እና ከገባበት አጣብቂኝ እራሱን ለማላቀቅ ሲል፤ “ወደ ብሔራዊ መግባባት ለመሄድ የሚያስችል እርምጃ እንወስዳለን” ብሎ ቃል በመግባት፤ እሰየው የሚያሰኝ፤ ስራዎች ሰርቷል። ከነዚህም ስራዎቹ፤ በርካታ የፖለቲካ እስረኞችን መፍታቱ እና፤ ከገዥው ፓርቲ የተለየ አመለካካት ያላቸውን፤ የሕዝቡን የልብ ትርታ በማዳመጥ መልስ መስጠት ለቻሉት ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ለዶ/ር አብይ አሕመድ መንበረ ሥልጣኑን መስጠቱ ነው።

ዶ/ር አብይ ሥልጣኑን ከመረከባቸው እና ከተረከቡም በኋላ ሃገራችንን አንድ የሚያደርግ እና ሕዝቡን የሚያስተባብር እና የሚያፋቅር መልክት ማስተላለፋቸው፤ የሃገራችንን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቅ የተለያይ እርምጃ መውሰዳቸው፤ የሕዝብ ድጋፍ እና ውዳሴም አስገኝቶላቸዋል። ብሩህ እና ባለራዕይ መሪ ስንል፤ ምን ማለት እንደሆነም በምሣሌ እና በተግባር አሳይተውናል። ይህ በጎ ጅማሮ፤ በአንድ ሰው ሥራና ድካም ብቻ ዘላቂና ስኬታማ ሊሆን አይችልም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ስለእርቅና ፍቅር እየሰበኩ ቢሆንም፤ ዘላቂ ሰላም ሊያመጣ የሚችለውን የብሔራዊ እርቅ አጀንዳ ተቋማዊ በሆነ መንገድ እየሰሩበት እንዳልሆነ ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ በኩል፤ እንደ እሳት አደጋ በየቦታው የሚነሳውን እሳት እያጠፉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሃገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ተጠምደው ብዙ ቦታዎች ተፍ ተፍ ሲሉና ሲደክሙም እያየን ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተደጋጋሚ ጥሪም አግዙኝ የሚል ነው። ታድያ፤ እንደ ተመልካች፤ ከመንገድ ዳር ሆነን ከበሮ ከመደለቅ፤ እና የሳቸውን ምስል የያዘ ካናቴራና ቆብ ከመልበስ ውጭ ማድረግ ያለብን ነገር የለም ወይ? ነፍሱን ይማረውና፤ ወዳጄ ዶ/ር አብይ ፎርድ፤ “ዲሞክራሲ ለሕዝብ ሥራ ነው” የሚላት ነገር ነበረችው። አዎ ዲሞክራሲ ስራን፤ መስዋእትነትን፤ የሕዝብን ተሳትፎ ይጠይቃል። ለዓመታት የብሔራዊ እርቅ አጀንዳ ፋና ወጊ ሆነው ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን፤ የዓለምን መንግስታት ሲጎተጉቱ የነበሩ ኢትዮጵያውያን፤ ዛሬ የት ሄዱብን? ለምንድነው፤ ብሔራዊ እርቅ እውን እንዲሆን ስራ ሲሰሩ የማናየው?

የብሔራዊ እርቅ አጀንዳን በተቋምነት መልክ አስይዞ፤ ሁሉም የሚሳተፍበት፤ ጉባኤ ለማድረግ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩን አመራርም ሆነ የመንግስታቸውን ስራ አይጠይቅም። ለዚህም እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በታህሳስ 1993 በአዲስ አበባ በግዮን ሆቴል የተደረገው፤ ገዥው ፓርቲ አሻፈረኝ ያለበት፤ ግን ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ ገዥው ፓርቲ የፈጠረባቸውን መሰናክል አልፈው፤ ስኬታማ የሆነ ስብሰባ አድረገው፤ “የኢትዮጵያ የሰላምና የዲሞክራሲ አማራጭ ኃይሎች ምክር ቤት” የተባለ ድርጅት የመሰረቱበት ጉባኤ፤ አሁንም እንደ አርአያነት ሊያገለግል ይችላል። ለታኅሳሱ የአዲስ አበባ ስብሰባ መሰረት የጣለው፤ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በመጋቢት 1993 ዓ.ም በተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ፓሪስ ላይ ስብሰባ ተደርጎ፤ በሃገራችን ብሔራዊ እርቅ እንዲኖር ገዥውን ፓርቲ ያካተተ የብሄራዊ እርቅ ስብሰባ እንዲደረገ በመወሰኑ ነው።

ለመጋቢቱ ስብሰባ ቁልፉን ሚና የተጫወተው፤ ያኔ የነበረው፤ ዛሬ ግን የከሰመው፤ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ኃይሎች ቅንጅት፤ በምኅፃረ ቃሉ ኢድኃቅ ተብሎ የሚታወቀው ድርጅት ነው። ኢድኃቅ በ1990 መኢሶን እና ኢሕአፓን በማስታረቅ የተመሰረት ድርጅት እና ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ እስከፈረሰበት ጊዜ ድረስ የገዥው ፓርቲ ራስ ምታት የነበረ ድርጅት ነው። ገና የፓሪሱ ስብሰባ ሲታቀድ፤ ገዥው ፓርቲ በከፍተኛ ፕሮፖጋንዳ የዘመተበትና፤ በሰላም እና እርቅ ጉባኤውም ላይ የመሳተፍ ፍላጎት እንደሌለው የገለፀበት ስለነበር፤ ገዥው ፓርቲ በዚህ ጉባኤ ላይ አዎንታዊ ሚና እንዲጫወት፤ በተለይም ውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፤ የአሜሪካን፤ የካናዳና፤ የአውሮፓ መንግሥታት፤ ገዥው ፓርቲ ላይ ጫና እንዲያደርጉ ከፍተኛ ግፊት በማድረግ፤ የሰላምና የእርቅ አካል እንዲሆን ብዙ ጎትጉተዋል። በዚህ አጋጣሚም፤ አባቴ፤ በወቅቱ የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ከነበሩት ከሚሥስ ኪም ካምቤል (Mrs. Kim Cambell) ጋር በመፃፃፍ፤ ለዚህ ጉዳይ ከካናዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መስርያ ቤት ሰው እንዲመደብ በማድረግ፤ የኢትዮጵያ ገዥው ፓርቲ በሰላም እና የእርቁ ጉባኤ እንዲሳተፍ ጫና ለማድረግ ከካናዳ መንግስት ጋር በቅርበት መሰራቱን ማስታወስ እፈልጋለሁ። በሃገር ውስጥም፤ የኢትዮጵያ ሕብ ገዥው ፓርቲ ላይ ግፊት እንዲያደርግ ከፍተኛ የቅስቀሳ ሥራ ተሰርቷል። ገዥው ፓርቲ ግን፤ ከጥግ እሰከ ጥግ የሚጮኽውን የኢትዮጵያውያንን ድምጽ ከመጤፍ አልቆጠረውም። ጥሪውን አወገዘ፤ አራከሰም፤ ጉባኤውን ለማኮላሸት፤ አፈ ቀላጢዎቹም ከአጥናፍ እስከአጥናፍ አሰማራ። ተቃዋሚው ግን ተስፋ ሳይቆርጥ ለጥቅምት 1993 አቅዶት የነበረውን የአዲስ አበባ የሰላም እና የእርቅ ጉባኤ፤ ለታኅሳስ አዘዋወረ። አሁንም ገዥውን ፓርቲ በጉባኤው ለማሳተፍ  ግፊቱ ጨመረ፤ ገዠው ፓርቲ ግን ከሃሳቡ ፈቀቅ አላለም። እንደውም የታኅሣሱን የአዲስ አበባ የሰላም እና የእርቅ ጉባኤ ለማደናቀፈ፤ በድፍረት እና ሊደርሰባቸው የሚችለውን መከራ ለመቋቋም ቆረጠው፤ ከአውሮፓና ከአሜሪካ ወደ ሃገራቸው የሄዱትን የሰላም እና የእርቅ ፋኖዎች፤ ከአዲስ አበባ አየር ጣብያ አሰራቸው። ይህ ገዥው ፓርቲ ከሰራቸው አብይ ስህተቶች አንዱ ነው ማለት ይቻላል።

ዛሬ ግን አዲስ ምእራፍ ተጀምሯል፤ የሰላም እና የእርቅ አካል ለመሆን ፈቃደኛ የሆነ የግዥው ፓርቲ አመራር አለ። አመራሩ ግን የግድ ጉባኤውን ማቀድ፤ መምራትም፤ ሆነ ማደራጀት አይጠበቅበትም። የሚጠበቅበት በዚህ ጉባኤ መሳተፍ እና ለሃገራችን ብሔራዊ እርቅ መሰረት መጣል ብቻ ነው። ዛሬ ያለውን ጥሩ አጋጣሚ ለመጠቀም፤ ተቃዋሚውም ሆነ ተፎካካሪው፤ እጁን አጣምሮ ለምን ይጠብቃል? እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1993 ዓ.ም አዲስ አበባ ተካሂዶ የነበረው የሰላም እና የእርቅ ጉባኤ እንደ አርአያ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል። ለ1993 የሰላም እና የእርቅ ጉባኤ እነ አቶ አበራ የማነአብ፤ መርሻ ዮሴፍ፤ ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ፤ ዶ/ር በየነ ጴጥሮስ የመሪነቱን ሚና ተጫውተዋል፤ ዛሬም፤ ይህንን የመሪነት ሚና ሊጫወቱ የሚችሉ ብዙ ብርቅዬ ኢትዮጵያውያን አሉ። ብሔራዊ እርቅን መተግበር እና “የሰላም እና የእርቅ ጉባኤ” ማካሄድ ጊዜ የማይሰጠው እጅግ አጣዳፊ ነው ብሎ ይህ ፀሃፍ ያምናል። ይህ ዶ/ር አብይን ወይም የገዥውን ፓርቲ አመራር የሚጠብቅ አይደለም። እኛም ስንነቀሳቀስ እና የበኩላችንን ስናደርግ ነው፤ ለዶ/ር አብይ አመራር ተግባራዊ ድጋፍ ልንሰጥ የምንችለው ብዬ አምናለሁ። ስለዚህ፤ የ1993 የአዲስ አበባው የሰላምና የእርቅ ጉባኤ እንደ አርአያነት ተወስዶ፤ ዛሬውኑ፤ “ለሰላም እና እርቅ ጉባኤ” -ለብሔራዊ እርቅ ስኬታማነት ተግባራዊ እንቅስቃሴ እናድርግ።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን ይባርክ።

Comments are closed, but trackbacks and pingbacks are open.