ዶ/ር ዐብይ አሕመድና የሕዳሴው ጉዞ። (ክፍል አንድ)

                                 ከጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ።

          “Leadership is not about the next election, it is about the next generation” Simon Sinek

         የእንግሊዝ ተወላጁ ደራሲ፤ ሳይመን ሲንክ፤ “መሪነት ስለቀጣዩ ምርጫ ማሰብ ሳይሆን፤ ስለቀጣዩ ትውልድ ማሰብ ነው” ይላል በግርድፉ ሲተረጎም። በተለይም ላለፉት 44 ዓመታት የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ በሃገሩ፤ ፍትሕ፤ ነፃነት፤ እንዲሁም ዲሞክራሲያዊ ስልተ ሥርዓት እንዲመሰረት ከፍተኛ ተጋድሎ አድርጓል። ምንም እንኳን፤ በግንቦት 1983፤ ተጠናቀቀ በተባለለት የእርስ በእርስ ጦርነት፤ ዲሞክራሲን፤ ፍትሕንና፤ ነፃነትን፤ “ለተጨቆነው ሕዝብ እናመጣለን” ባሉን ግለሰቦች እና የፖለቲካ ድርጅቶች በትረ መንግሥቱ ቢጨበጥም፤ ለነፃነት፤ ለፍትሕ፤ እና ዲሞክራሲያዊ ስልተ ስርዓት መገንባት፤ ጭዳ የሆነው የሃገሬ ወጣት መስዋእትነት ተዘንግቶ፤ ከ17 ዓመታቱ የወታደራዊ ስርዓት በከፋ መልኩ ላለፉት 27 ዓመታት ስንታሰር፤ ስንሰደድ እና ስንገደል፤ እንዲሁም ለሰሚ በሚዘገንን ስቃይ ውስጥ ኖረን፤ ያ 44ቱ ክፉ የአገዛዝ ዓመታት አበቃ የምንልበት አፋፍ ላይ ደርሰን፤ ሃገራችን የሕዳሴ ጉዞ ጀምራለች።

ከዛሬ 8 ዓመታት በፊት “Tear Down the Wall” “ግድግዳውን አፍርሱ” በሚል ርዕስ ባስነበብኩት የእንግሊዝኛ መጣጥፍ እንዲህ ብዬ ነበር፤

“To contribute our fair share for the wellbeing of our nation and to end the cycle of violence, it is profoundly important for the elites to Tear Down the Walls that they have built in order to debunk one another. By demonizing one another, the path to empower our people will not be established. The future generation expects more than good writings; it expects us to hand over a system of government that allows our people to be governed by their consent. The future generation expects us to pass it to them a civilized way of dealing with each other. There will always be disagreements; there are going to be conflict of ideas and interests; the wisdom or the lack there of is the way we handle conflicting ideas and interests. We may continue to bark at each other in cyber space or choose to come together with all our disagreements and create a conducive atmosphere to deal with each other in a manner that is productive and responsible.”

ሙሉውን ለማንበብ ከፈለጉ’ ይህን ሊንክ ይጠቀሙ፤ http://www.ethiosun.com/archives/13511

በግርድፉ ሲተረጎም፤“ለሃገራችን ደህንነት የበኩላችንን ለማበርከት እና፤ የግጭትን አዙሪት ለመስበር፤ምሁሮቻችን አንዳቸው ሌላውን ለመጣል የገነቡትን ግድግዳ ማፍረስ እጅግ አስፈላጊ ነው። አንዳችን ሌላችንን በመኮነን፤ ሕዝባችንን የሥልጣኑ ባለቤት ሊሆን የሚችልበትን መንገድ መገንባት አንችልም። ቀጣዩ ትውልድ፤ ከጥሩ ጽሁፎች የተሻለ ነገር እንድናስረክበው ከእኛ ይጠብቃል፤ ሕዝቡ በራሱ ፈቃድ እና ፍላጎት የሚያስተዳድረው የስልተ ሥርዓት ዘይቤ እንድናስረክብ፤ ቀጣዩ ትውልድ ከእኛ የሚጠብቀው ነው። ቀጣዩ ትውልድ፤እንዳንስተላልፍለት የሚጠብቀው እሴት፤ አንዳችን ከሌላችን ጋር የምናደርገው ግንኙነት በሰለጠነ መልክ እንዲሆንም ጭምር ነው። በመካከላችን፤ ሁሌም አለመሰማማት ይኖራል፤ የሃሳብ ግጭቶች እና የፍላጎቶቻችን ልዩነቶች ሁሌም ይኖራሉ፤ ብልህ ወይም ብልህ አልባ የሚያደርገን ግን የምንጋጭባቸውን ሃሳቦች እና ፍላጎቶች የምንፈታባቸው መንገዶች ናቸው። አማራጫችን፤ በየድህረ ገፆች ላይ አንዳችን ሌላችንን ላይ ማንቧረቅ ወይም ደግሞ፤ ያሉንን ልዩነቶቻችንን እንደያዝን፤ አንዳችን ከሌላችን ጋር የምናደርገው ግንኙነት ውጤታማና ሃላፊነት በተሞላበት መልኩ እንዲሆን ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ይሆናል።”  የሚል ነው።

በየትኛውም ሃገር፤ ለነፃነት በሚደረግ ትግል፤ የሃገሬው ምሁራን የሚጫወቱት ሚና ትልቅ ነው። ዛሬ ለተጀመረው፤ የሕዳሴ ጉዞ፤ የኢትዮጵያ ምሁራን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፤ ከፍተኛ መስዋዕትነትም ከፍለውበታል። ገዥው ፓርቲ፤ በተደረገበት ከፍተኛ ግፊት፤ የሚሄድበት አቅጣጫ ስለጠፋው፤ ሳይወድ በግዱ፤ላለፉት 27 ዓመታት የተጓዘበትን አደገኛ አቅጣጫ ሊለውጡ ለሚችሉ፤ ከውስጡ ለወጡ የለውጥ ሃዋርያዎች ቦታ በመልቀቅ፤ ዛሬ፤ ከብሔርተኝነት ይልቅ የኢትዮጵያዊነት ማንነት ጎልቶ ሊታይ ችሏል። ምንም እንኳን የዚህ የሕዳሴ ጉዞ ውጤት፤ የሚሊዮኖች ትግል እና የመስዋዕትነት ውጤት ቢሆንም፤ በተለያየ ሁኔታ ማየት እንደሚቻለው፤ ለውጡን ስኬታማ ለማድረግ እና፤ ከሚጠበቅበት ግብ ለማድረስ፤ ሃላፊነቱ እና ሥራው የተጣለው በጣም በጥቂት ሰዎች ላይ ነው። ብዙዊች፤ አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስቴር “ከእግዚአብሔር የተላከ ነው” በሚል ፈሊጥ፤ ሁሉም ነገር በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲለውጥ፤ እጃቸውን አጣጥፈው፤ ለውጥ ከጠቅላይ ሚኒስቴሩ ብቻ ሲጠብቁ እያየን ነው። የጀመርነው ጉዞ ከፍተኛ ተስፋ ሰጭ የመሆኑም ያክል፤ ብዙ ስጋቶችንም ጭሯል። ሌላው ቀርቶ አንቱ የተባሉ ምሁሮቻችን፤ በጭንቅላታቸው በማሰብ፤ የተጀመረውን የሕዳሴ ጉዞ አቅጣጫ ለማስያዝ ገንቢ ሃሳብ ከማቅረብ እና አስፈላጊውን ንድፈ ሃሳብ ከማዝጋጀት ይልቅ፤ በማያስፈለጉ መላ ምቶች ተጠምደው፤ አጋጣሚውን “ጠላት” ብለው የፈረጇቸውን “የፖለቲካ ባላንጣዎቻቸውን” ለማብሸቅ፤ ለማሸማቀቅ እና ለማዋረድ ሲተጉ ማየት፤ እጅግ ልብ ይሰብራል።

በቅርቡ የተከበሩ ዶ/ር ጌታቸው ኃይሌ፤“ክቡር የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ እንኳን ደኅና መጣህ” በሚል ርዕስ በማህበራዊ ገፆች ላይ ባስነበቡት ጽሁፋቸው፤ መካሪ ሃሳብ ያቀረቡ ቢሆንም፤ ቀልቤን ከሳቡኝ አባባላቸው አንዱ {ዶ/ር አብይና፤ አቶ ለማ መገርሣ}“በምታዘጋጁት ገለልተኛ ምርጫ ፓርቲዎች ሲወዳደሩ እንድታዩና ይኸን ትልቅ ታሪክ ለመሥራት የጠራችሁን አምላክ ነፃ ከአወጣችሁት ሕዝብ ጋራ ስታመሰግኑት ልናይና ልንሰማ እንመኛለን” (መስመር እና ድምቀት የተጨመረ)። ይህ ዓይነት አመለካከት እና ሃሳብ፤ የሚንፀባረቀው፤ በክቡር ዶ/ር ጌታቸው ኃይሌ ብቻ ሳይሆን፤ በበርካታ ምሁራን መሆኑ፤ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ “አግዙኝ” እያሉ የሚማጸኑት መልዕክት ሰሚ አለማግኘቱን ጠቋሚ ነው። በተለይም በብዙ የጠቅላይ ሚኒስቴሩ ቲፎዞዎች የተዘነጋው እና ቀለል ተደርጎ የሚነገረው ነገር፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩና አቶ ለማ መገርሣ “ሕዝቡን ነፃ አወጡት” እየተባለ የሚነገረው የተሳሳተ ውዳሴ ነው። ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር ዐብይ በሃገራችን የተጀመረውን ለውጥ አቅጣጫ ለማስያዝ ሌት ተቀን የሚያደርጉት ጥረት፤ እጅግ የሚደነቅ እና የሚበረታታ፤ እንዲሁም የሌሎቻችን አገዝ የሚያስፈልገው ነው። ነገር ግን፤ ስንት መስዋእትነት ከፍሎ፤ ከተጣለበት የግፍ ቀንበር እራሱን ነፃ ያወጣውን ሕዝብ፤ “ነፃ አወጡሕ” ብሎ መመፃደቅ፤ የሚያሳፍር እና፤ ለዚህ የነፃነት ብርሃን ሕይወታቸውን የገበሩትን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች፤ ትግላቸውንም መስዋዕትነታቸውንም ማራከስ ነው። በትግሉ ማዕበል ተገፍተው፤ ከገዥው ፓርቲ ውስጥ፤ የለውጥ ሃዋርያዎች አንገታቸውን ቀና እንዲያደርጉ ፈር የቀደዱትን አቶ ለማ መገርሳን ከተጫነባቸው ኢሕአደጋዊ የከሸፈ አስተሳሰብ ነፃ ያወጣቸው ሕዝቡ ሆኖ ሳለ፤ ሕዝቡን ነፃ አወጡ ማለት የተሳሳተ ነው። እነ አቶ ለማ መገርሣን ተከትለው፤ በለውጡ “ፀበል የተጠመቁት” እነ ዶ/ር ዐብይ፤ ለ27 ዓመታት ሲከተሉት እና ሲስብኩት ከነበረው የዘር ፖለቲካ አስተሳሰብ ነፃ ያወጣቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። እነሱ ሕዝቡን “ነፃ እንዳላወጡት” በጽኑ ሊሰመርበት የሚገባ ጭብጥ ነው። ይህ እውነታ ሳይበረዝ በታሪክም ሊመዘገብ ይገባዋል።

ከክቡር ዶ/ር ጌታቸው ኃይሌ ጽሁፍ እና ከሌሎች ምሁራን የሚንፀባረቀው አመለካከት፤ እንዲሁም በማህበራዊ ገጽ የሚደረጉ “ውይይቶችም” እንደሚያሳብቁት፤ ብዙዊች፤ በድጋፍ ሰልፍ፤ በድጋፍ ስብሰባ፤ የድጋፍ ኮሚቴ በማቋቋም፤ ዶ/ር ዐብይን የሚያወድሱ መፈክሮች በመፃፍ፤ ቲ-ሸርት እና ኮፍያ በማሰራት ጊዜ ሲያሳልፉ ከማየት ባሻገር፤ የተለያዩ ተቋማትን ለመገንባት የሚያስችል እንቅስቃሴ ሲያደርጉ እየተመለከትን አይደለም። በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሃገር ያሉት ተቃዋሚ (ተፎካካሪ) ድርጅቶች፤ ላለፉት አራት ወራት ሰሩ የምንላቸው ቁም ነገሮች ምን እንደሆነ ለዚህ ፀሃፍ ግልጽ አይደለም። ብዙዎች ሕወሃትን ከማውገዝ፤“ግልጽ ደብዳቤ” በሚል ርዕስ ስለክልል መፍረስ፤ ስለባንዲራ፤ ስለ ሽግግር መንግስት መቋቋም፤ ስለ ሕገ መንግስቱ መቀየር፤ እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአደጋ እራሳቸውን እንዲጠብቁ ከመፃፍና “ከመምከር ባሻገር” የብሔራዊ እርቅ ሊደረግ የሚችልበትን ስልት ሲጠቁሙ፤ የሃገሪቱ የፍትሕ ስርዓት ሊስተካከል የሚችልበትን መንገድ ሲያሳዩ፤ ሃገሪቱን ከምርጫ ባሻገር፤ ወደ ዲሞክራሲያዊ ስልተ ስርዓት ሊያራምዷት የሚችሉ ተቋማትን በመገንባት ረገድ መደረግ ስላለባቸው ነገሮች በጥናት የተደገፈ ንድፈ ሃሳብ ሲያቀርቡም እያየን አይደለም።

አሁን እያይን ያለነው ጥገናዊ ለውጥ፤ መሰረታዊ እና ስር ነቀል በሆነ ለውጥ እንዲተካ፤ የሚሰነዘሩ እና አቅጣጫ የሚያሲዙ ሃሳቦችም እየተመለከትን አይደለም። እንደውም ጠቅላይ ሚኒስቴሩ፤ ሎስ አንጀለስ ከኢትዮጵያውያን ጋር ባደረጉት ውይይት ስለ ሥር ነቀል ለውጥ ለተጠየቁት ጥያቄ፤‘ሁሉንም ነገር ከሥሩ ነቅለን ጥለነዋል፤ የሚያስፈልገን የተዘረፈውን ነገር መልሰን መትከል ነው’ ብለው ሲመልሱ፤ የሚያጨበጭቡ እጆችን እንጂ፤ የሚያስተውሉ ሕሊናዎችን አለማየት፤ የአስተሳሰብ ለውጥ አብዮት እንደሚያስፈልገን ያስረዳል። በነፈሰበት የመንፈስ ስሜታችንን ተቆጣጥረን፤ ጠቃሚ በሆኑ ሃሳቦች ላይ በአላማ ጽናት ልንሟገት ይገባል። ብዙውን ጊዜ አንዳንድ ነገሮችን ሳናስተውል፤ ለጆሮ ስለሚጥም ብቻ መልሰን እናስተጋባቸዋለን፤ በተለይ የምንደግፈው ሰው የሚናገረውን ነገር፤ መልዕክቱ እና የሚያስከትለው ጥቅምም ሆነ ጉዳት ሚዛን ውስጥ ሳይገባ እንዲሁ የመደገፍ ብቻ አዝማምያም አለን። እንደ አቶ መለስ ደጋፊዎች፤ የዶ/ር ዓብይም ደጋፊዎች፤ እሳቸው ሲያነጥሱ፤ ማህረብ ለማቀበል ብቻ የምንጣደፍ ከሆነ፤ ከሃይል ሚዛን በስተቀር ያስተሳሰብ ለውጥ አልተደረገም ለማለት ያስደፍራል። ጊዜው የሚጠይቀው፤ በልባችን ብቻ ማሰብን ሳይሆን፤ ወይም “ሕዝብ ለደገፈው መሪ”፤ የሚለውንም ሆነ የሚሰራውን ሙሉ ለሙሉ (unconditionally)መደገፍ አለብን ከሚል ጮርቃ ስሜት ሳይሆን፤ አእምሮዋችንን በማሰራት፤ ይህ በሕዝብ ትግልና ድል የተጀመረው የሕዳሴ ጉዞ፤ ሳይደናቀፍ፤ ሕዝብን የሥልጣኑ ባለቤት የሚያደርገበትን አቅጣጫ ማስያዝ ይጠበቅብናል። (ክፍል ሁለት ይቀጥላል)

Comments are closed, but trackbacks and pingbacks are open.