ግልጽ ደብዳቤ፤ (የግል ጉዳይ) (ለኤምባሲው በኢሜል እና ፋክስ የተላከ)

ሰኔ 14 ቀን 2010 (June 21, 2018)

ለተከበሩ፤ አምባሳደር ካሳ ተክለብርሃን፤ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ሪፓብሊክ መንግስት አምባሳደር በአሜሪካ።

ክቡርነትዎ፤ ይህንን ደብዳቤ እንድጽፍ ያስገደደኝ፤ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በሰኔ 19 ቀን 2015 ዓ.ም.፤ ፓስፖርቴን ለእድሳት ዋሽንገተን ዲሲ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጽ/ቤት ከሰጠሁ በኋላ፤ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ፤ ፓስፖርቴ ታድሶ መመልስ ሲገባው፤ ፓስፖርቴ ሳይመለስልኝ ሶስተኛ ዓመቱን በመያዙ ነው። ፓስፖርቴን ለእድሳት በሰጠሁበት ወቅት፤ ከእኔም ጋር ፓስፖርታቸውን ለእድሳት የሰጡ ሌሎች ኢትዮጵያውያንም አብረውኝ ነበሩ። የእነዚህን ኢትዮጵያውያንን ፓስፖርት አድሶ ለመመለስ፤ የኢትዮጵያ መንግስት የወሰደበት ጊዜ ከሶስት ወር በታች ነው። ፓስፖርቴ ታድሶ ይመለሳል በማለት በተስፋ ብጠብቅም፤ እስካሁን ግን አልተመለሰም። ይህንን ጉዳይ በተመለከተም፤ ቀድም ብሎ በእርሶ ቦታ አምባሳደር ለነበሩት፤ ለአምባሳደር ግርማ ብሩ፤ በተደጋጋሚ ደብዳቤ ብጽፍምና፤ ለኤምባሲው በተደጋጋሚ የላኩት ኢሜል፤ እንዲሁም የፋክስ መልእክት፤ እንዲሁም ደግሞ ለኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መስርያ ቤት የላኳቸው ደብዳቢዎች፤ ምንም ምላሽ ያልተሰጣቸው በመሆኑ፤ ዛሬም ይህንን ደብዳቤ ለመፃፍ ተገድጃለሁ።

ምንም እንኳን ፓስፖርታቸው ታድሶ ከተመለሰላቸው ቀደም ብዬ ከጠቀስኳቸው ኢትዮጵያውያን፤ እኔን ለየት የሚያደርጉኝ ሁለት ነገሮች እንዳሉ ብገነዘብም፤ በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት እራሱ አርቅቆ ያፀደቀውን ሕገ መንግሥት አንቀፅ 6ን በመጣስ የዜግነት መበቴን ለመንፈግ የሚያስችል ምንም ዓይነት ሕጋዊ መሰረት የለውም። የፓስፖርቴን እድሳት ስከለከል ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። በመጀመርያው ጊዜ፤ የፓስፖርቴ አለመታደስ፤ ለቀድሞው አምባሳደር፤ ከቡር አምባሳደር ብርሃኔ ገ/ክርስቶስ፤ አሁን ስማቸውን መጥቀስ በማልፈልጋቸው ግለሰቦች፤ ያለእኔ ጠያቂነት፤ አቤቱታው በመቅረቡ፤ ፓስፖርቴ ሊታደስ ችሏል። ያኔም፤ ፓስፖርቴ እንዳይታደስ ሕገ ወጥ እርምጃ የተወሰደው፤ “የማንንም ኢትዮጵያዊ የዜግነት መብት የመንጠቅ ሥልጣን አለን” ብለው በሚያምኑ፤ እራሳቸውን ከሕግ በላይ ባደረጉ የፓርቲና የመንግስት ባለስልጣናት መሆኑ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ “የሕግ የበላይነት” የሚለው ቃለ-ሃረግ ከመፈክር ያላለፈ ባዶ ቃል መሆኑን ያረጋገጠ ነው። እኔ ብቻ ሳልሆን፤ በሺህ የሚቆጠሩ፤ ትውልደ ኤርትራዊ ኢትዮጵያውያንና የኤርትራ የዘር ሃረግ ያላቸው ኢትዮጵያውያን፤ የኢትዮጵያዊ ዜግነት መብታቸውን ተገፈው፤ እንደ-ወንጀለኛ፤ በሌሊት ከቤታቸው ተወስደው፤ ወደ ኤርትራ ተግዘዋል፤ ታስረዋል፤ ታፍነው የደረሱበት እንዳይታወቁ ተደርገዋል፤ ተገድለዋል፤ ደከመው ያፈሩት አንጡራ ንብረታቸውም ተዘርፏል። ከእነዚህም አንዷ ተበዳይ ወላጅ እናቴ ናት። በዕድልና በአጋጣሚ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የቀሩትም፤ ከሥራ ገበታቸው ተፈናቅለው፤ ከእነቤተሰባቸው በረሃብ አለንጋ እንዲቀጡ፤ በውርደት፤ በመሸማቀቅና፤ በፍርሃት እንዲኖሩ ተደርገዋል። የዚህ አሰቃቂ ግፍና በደል ጽዋ የደረሰባቸው፤ እርጉዝና ደካማ ሴቶች፤ ደካማ አዛውንቶችና፤ ነፍስ ያላወቁ ህፃናትም ጭምር መሆናቸው፤ እርሶ የሚውክሉት መንግስት የፈጸመውን ወንጀል የበለጠ ዘግናኝ ያደርገዋል። መንግስትዎ የፈጸመው ወንጀል፤ በኢትዮጵያዊነታችን ጽኑ እምነት ያለንን “ትውልደ-ኤርትራውያንን”፤ የተፈታተነ፤ ለኢትዮጵያ አንድነትና እድገት፤ ለሕዝቦቿ መብት መከበርና ነፃነት ያደረግነውን ትግልና፤ ትንሽም ትሁን ትልቅ፤ የከፈልነውን መስዋዕትነትና ያበረከትነውን አስተዋጽኦ እንድንጠይቅ ያደረገና ስሜታችንን እጅግ የተፈታተነም ነበር። የተወሰኑትም፤ ተስፋ ቆርጠው፤ ዜግነታቸውን ቀይረዋል። መንግስትዎና ሻዕቢያ በመመሳጠርና በመተባበር በኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ላይ ለፈጸሙት ወንጀልና ግፍ፤ ንፁሃን ዜጎች እጅግ ውድ ዋጋ ከፍለናል።

ትውልዴ ኤርትራ ውስጥ መሆኑ፤ ፓስፖርቴን ላለማደስ፤ ለመንግስትዎ ሰበብ ቢሆንም፤ ዋናው ምክንያት፤ ፓርቲዎና መንግስትዎ፤ የሚከተሏቸውን አደገኛ ፖሊሲዎች፤ የምታራምዱትን የዘር ፖለቲካ፤ ከሻዕብያ ጋር የተደረገውን ፀረ-ኢትዮጵያ ትብብር፤ ኢትዮጵያ ውስጥ አላባራ ያለውን የሰብዓዊ መብት ረገጣና ኢዲሞክራሲያዊ አምባገነን ሥርዓት፤ ከጅምሩ፤ በጽኑና በአደባባይ ስቃወምና ስታገል የቆየሁ በመሆኔ፤ እኔንና እኔን መሰል ሰዎች “ለማስፈራራት” የተወሰደ እርምጃ ለመሆኑ ምንም አልጠራጠርም። ያኔም አላማው ይህ ነበር፤ ዛሬም ዓላማው ይህ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ከኖርኩባቸው ጊዜያት፤ በስደት በአሜሪካን ሃገር የኖርኩባቸው ጊዜያት በእጥፍ ይበልጣል። በሃገሬ መንግስት፤ ገና በጨቅላ እድሜዬ ታስርያለሁ፤ ተቀጥቅጫለሁ፤ ዕድሜዬ ገና 15 ዓመት በነበረበትም ጊዜ፤ እኔና ጓደኞቼ፤ “በመንግስታችን” እንድንገደል ተወስኖብን፤ በሰዎች ጣልቃ ገብነት ሕይወታችን በመትረፉ፤ ሳንወድ በግዳችን፤ ለስደት ተዳርገናል። “የሃገሬ መንግስት” በምለው አካል፤ ይህ ሁሉ ግፍ ሲፈጸምብኝ፤ ኢትዮጵያዊ ስሜቴን አልሸረሸረውም። አለቆችዎ፤ ድልድይ ሲያፈርሱ፤ ሰላማዊ ዜጎች ሲጨፈጭፉ፤ ሰላማዊ ዜጎች እንዲራቡ፤ የእህል ክምችትና እህል የጫኑ መኪናዎች ሲያቃጥሉ፤ ከሻዕብያ ጋር ተመሳጥረው፤ ኢትዮጵያንና ኢትዮያዊነትን ሲሸረሽሩ፤ እኔና ጓደኞቼ ረሃብተኛውን በመመገብ፤ ያልተማረውን በማስተማር፤ በልማት አውታሮች እየተሳተፍን ሃገር እንገነባ ነበር። አለቆችዎ፤ ምሽግ ተደብቀው ጥይት ሲተኩሱ፤ ቦምብ ሲጥሉና፤ ከፋሽስታዊ ደርግ ጋር ሲታገሉ፤ እኔና ጓደኞቼ፤ ደርግ አፍንጫ ስር ሆነን፤ ማንንነታችንን ሳንደብቅና፤ ምሽግ ሳንቆፍር፤ ሕይወታችንን አደጋ ላይ ጥለን፤ በምንችለው አቅም ሁሉ ተፋልመናል።

ክቡርነትዎ፤ ይህንን የምነግርዎት ያለምንም ምክንያት አይደለም፤ የኢትዮጵያዊነት ዜግነት መብቴ በፍላጎት የመረጥኩት፤ ማንም ያልሰጠኝ፤ ውስጤ ያለ፤ ፍፁም በቃላት ሊገለጽ የማይችል ስሜት መሆኑን እንዲገነዘቡና፤ መንግስትዎ “የዜግነት መብቴን እንዲነጥቅ” የማልፈቅድ መሆኔን፤ መብቴን ለማስከበር ማድረገ ያለብኝን ሁሉ እንደማደርግ እንዲገነዘቡልኝ ነው። ይህ የመጀመርያ እርምጃዬ አይደለም፤ የመጨረሻዬ ይሆናል ብዬ ግን አምናለሁ።

ቀደም ብዬ፤ ከሁለት ዓመት በፊት ለኤምባሲው በፃፍኩት ደብዳቤ፤ የዜግነት መብቴን ለማስከበር፤ የግል እርምጃዬን እንደምወስድ ገልጫለሁ። ይህን ሕገ ወጥ ድርጊት ለሕዝብ ማሳወቅ የመጀመርያዬ እርምጃ ስለሆነ፤ የዚህን ደብዳቤ ግልባጭ፤ በማህበራዊ ድኅረ ገፆች ላይ አወጠዋለሁ። ቀጣዩ እርምጃዬ ምን እንደሚሆንም ቀደም ብዬ ስለገለጽኩ መድገሙ አስፈላጊ አይደለም።  መንግስትዎ፤ ዜጎችን በማስፈራራት፤ በማሰር፤ በማፈንና በመግደል፤ ለዜጎች ዲሞክራሲያዊ መብትና ነፃነት የሚደረገውን ትግል የሚያቆም መስሎ ይታየው እንደነበር በቀደምት ደብዳቢዎቼ ገልጫለሁ። ይህ ላይሆን እንደቻለ ግን፤ ዛሬ እኔም፣ እናንተም እያይነው ነው። ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ የተሰነቀው አዲስ ተስፋ፤ እንደ እኔ ዓይነት ዜጎችንም “ከእስር ነፃ” ያወጣል የሚል እምነት አለኝ። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚታየው ብሩህ ተስፋ፤ የገዘፈና የተወሳሰበ ፈተና አንፃር፤ የእኔን የደቂቁን አንድ ዜጋ ጉዳይ ትኩረት እንዲያገኝ መጠየቅ ተገቢ ላይሆን ይችላል። ይህ ጉዳይ ግን በእኔ ላይ ብቻ የተደረገ ላለመሆኑ፤ እርሶም መንግስቶም ያውቃል። የዚህ ጉዳይ አደባባይ ላይ መውጣት፤ ሌሎችንም አደባባይ ላይ እንዲወጡ ያበረታታል የሚል እምነት አለኝ። ዛሬ፤ ከጨለማው እስር ቤት እየወጡ በአገዛዙ ስለደረሰባቸው ፍጹም ሰብዓዊነት በጎደለው ተግባር የደረሰባቸውን ግፍ ከሚናገሩ ብርቅዬ ዜጎች አንፃር፤ እኔ ላይ ደረሰ የምለው የመብት ጥሰት ጋር በጣም ኢምንት መሆኑ ይሰማኛል። ሆኖም፤ ለራሴም የግልና የዜግነት መብት መቆም እንዳለብኝ ስለሚሰማኝም ነው፤ ይህንን መልዕክት ለማስተላለፍ የተገደድኩት።

ላለፉት 27 ዓመታት፤ በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት ያረጋገጠው ነገር ቢኖር፤ ሕዝብን መፍራት ሲገባው፤ ሕዝብ እንዲፈራው፤ ሕዝብን ማገልገል ሲገባው፤ ሕዝብ እንዲያገለግለው የሚፈልግና ከሕግ በላይ የሆነ፤ ደርግን የተካ ሌላ የከፋ ደርግ መሆኑን ነው። ያደረጋችሁት እና የወሰዳችሁት ጭካኔ የተመላው የማስፈራራት እርምጃ አልሰራም። የወሰዳችሁት አስከፊ እርምጃ ለዜጎች መብት የማሰማውን ጩኸት ሊያስቆም አልችልም። በአቶ ለማ መገርሣ አባባል “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው”። ለእኔ ግን ሕልውናዬም ጭምር ነው። የኢትዮጵያዊነት ዜግነቴን ማንም አልሰጠኝም፤ ማንም ደግሞ እንዲነጥቀኝ የማልፈቅድ መሆኔን አረጋግጥሎታለሁ። ስለዚህ በሰኔ 12 ቀን 2007 (June 19 2015) ለእድሳት የሰጠሁት ፓስፖርቴ፤ ታድሶ እንዲመለስልኝ፤ እጠይቃለሁ።

ከማክበር ሰላምታ ጋር፤

ጥበበ ሣሙኤል ፈረንጅ።

Please lend your support by writing  a letter to the Ethiopia Embassy at the following address:

Ethiopia Embassy

or The Ethiopian Ministry of Foreign Affairs

Fax: +251-11-5536325

Thank you for your support.

Comments are closed, but trackbacks and pingbacks are open.