አማርኛ

የአሜሪካን የገቢ ታክስ፤ ሀሁ እና አቡጊዳው፤

በጥበበ ሣሙኤል ፈረንጅ። ከፈል ፩

 

ላለፉት 29 ዓመታት፤ አሜሪካን ሃገር የግልና የኩባንያ የገቢና ሌሎች ታክሶችን (ግብር) በማዘጋጀትና ፋይል በማድረግ ሙያ ላይ ተሰማርቼ በዙ ነገሮችን ለማየት ችያለሁ። በአሜሪካን ሃገር የማህበረሰባችን ቁጥር ሲያድግ፤ በሙያው ውስጥ የተሰማሩ ሰዎችና፤ ግብር አሰሪዎች ቁጥር ከመጨመሩም በላይ፤ በየጊዜው የሚወጡ አዳዲስ የፌደራልና የስቴት ታክስ ሕጎችም፤ የታክስ ስራውን የተጠላለፈና ጥንቃቄ የሚጠይቅ ሥራ አድርጎታል። የገቢ ታክስ፤ እራሱን የቻለ ሰፊ ዘገባን የሚጠይቅ ነው። ሆኖም፤ በተለይ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ፤ በማህበረሰባችን ውስጥ፤ በተጠቃሚው እና ሙያው አለን በሚሉ ተቋሞችና ግለሰቦች በርካታ ስህተቶች ሲስሩ በማየቴ፤ በተለይ ተጠቃሚው ግብርን (ታክስን) አስመልክቶ መሰረታዊ የሆኑ ነገሮች ላይ ግንዛቤ እንዲኖረው ይህችን መጣጥፍ ለመጫር ተገድጃለሁ።

በአሜሪካን እየተለመደ የመጣው፤ የታክስ ጊዜ ሲደርስ፤ ሁሉም ተመላሽ ገንዘብ የሚጠብቅ መሆኑ ነው። ተመላሽ ገንዘብ መጠበቅ ብቻ ሳይሆን፤ በሺህ የሚቆጠር ገንዘብ ተመላሽ ካልሆነ፤ የሚቆጡ ሰዎች አጋጥመውኛል። አንዳንድ ሰዎች፤ ተመላሽ (refund) ይኑራቸው አይኑራቸው ሳያውቁ፤ ተመላሽ አለን ብለው የሚገምቱትን የገንዘብ መጠን፤ ባጀታቸው ውስጥ የሚያካትቱም አጋጥመውኛል። ስለአሜሪካን የገቢ ታክስ ሕግ ግንዛቤ ለማግኘት መጀመርያ ታክስ ምንድነው የሚለው መመለስ ያለበት ጥያቄ ነው።

የታክስ ዋና ዓላማ፤ የፌደራል፤ የስቴት ወይም የከተማ፤ መንግስታት፤ ከዜጎች ገቢ ለመሰብሰበ የሚደነግጉት ሕግ ነው። የታክስ ሕግ የወጣበት ዋና ምክንያት፤ መንግስታት ገንዝብ እንዲሰበስቡ እንጂ፤ ለዜጎቻቸው ገንዘብ ለመስጠት አይደለም። መንግስታት በሚሰበስቡት ታክስ፤ ለሕብረተሰቡ የተለያዩ መሰረት ልማቶችን ይገነባሉ፤ ለመንግስት ሠራተኞች ደምውዝ ይከፍላሉ፤ መንግስት ስራውን እንዲሰራ ለሚያደርጉ ነገሮች ሁሉ ይከፍላሉ። የታክስ፤ መሰረታዊ ዓላማ ይህ ነው። የአሜሪካንን የታክስ ሕግ ከሌሎች ሃገራት ለየት የሚያደርገው፤ ታክስ ከፋዩ መክፈል የሚገባውን ታክስ ሊቀናንስ የሚችልበት የተለያዩ መንገዶች (ዘዴዎች) በሕግ የተካተቱ መሆናቸው ነው። ሆኖም እነዚህን ዘዴዎች ከሕግ ውጭ የሚጠቀሙ ባለሙያዎችና ተጠቃሚዎች በመኖራቸው፤ እንዲህ ዓይነት ጥፋት ፈፃሚዎችን ለመቅጣት፤ መንግስት ሕግ አውጥቷል። ለዚህም ነው ታክስ ሲሰራ፤ ከሕግ አኳያ መሰራቱን ተጠቃሚው ማረጋገጥ ያለበትና፤ የሚያገኘውን ተመላሽ ከፍ ለማድረግም ሲባል፤ ባለሙያውን መግፋት የሌለበት። ምንም እንኳን፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፤ መንግስት ባለሙያዎችን ተጠያቂ የሚያደርግ ሕግ ቢደነግግምና፤ በርካታ ባለሙያዎችም፤ ፈቃዳቸውን ከመነሳት ጀምሮ፤ ለረጅም ጊዜ እስከመታሰር የሚያደርስ ቅጣት ቢበየንባቸውም፤ ተጠቃሚው ከመጠየቅ ወይም ለቅጣት ከመዳረግ አያልፍም። ዞሮ ዞሮ ዋና ተጠያቂው፤ ተጠቃሚው ነው።

ቀድም በዬ እንድገለጽኩት፤ የታክስ ሕግ ዋና ዓላማው መንግስት ገንዘብ መሰብሰብ እንዲችል ነው። በዚህ በታክስ ሕግ ውስጥ ከተካተተው አንዱ ህግ፤ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች፤ ለመርዳት፤ መመዘኛውን ለሚያሟሉ ተጠቃሚዎች መንግስት የሚሰጠው ገንዘብ ወይም ተመላሽ (refund) ነው። በርከት ያለው ተጠቃሚ ተመላሽ የሚያገኘው፤ የተለያዩ ሕጋዊ የሆኑ ታክስ ክፍያ መቀነሻ ዘዴዎችን በመጠቀም የታክስ እዳውን ማሳነስ ሲችል ነው። ሁሉም ደሞዝተኛ፤ ከደሞዙ ላይ አራት ዓይነት ታክስ ይቀነስበታል (ይቆረጥበታል)። እነዚህም፤ (1) የፌደራል የገቢ ታክስ (2) የሜዲኬር ታክስ (3) ሶሻል ሴኪዩሪቲ ታክስ እና(4) የስቴት ታክስ ናቸው። ለገቢ ታክስ፤ ሂሳብ በየዓመቱ በሚወራረድበት ጊዜ ለአማካኝ ተጠቃሚው፤ የሜዲኬር ታክስና የሶሻል ሴኪዩሪቲ ታክስ ከሂሳብ ውስጥ አይገቡም (ክ150 ሺህ ብር በላይ ገቢ ላላቸው ተጠቃሚዎች ሂሳብ ውስጥ የሚገቡበት ወቅት አለ፤ ይህ እራሱን የቻለ ርእስ ስለሚፈልግ ዘለዋለሁ)። አብዛኛው ተጠቃሚ ተመላሽ የሚያገኘው፤ በዓመት መጨረሻ ሂሳብ ሲወራረድ (ታክስ ፋይል ሲደረግ) ተጠቃሚው፤ ለስቴቱም ሆነ ለፌደራል መንግስት መክፈል ከሚገባው በላይ ከደሞዙ ከተቆረጠበት ነው። ተጠቃሚው መክፈል ከሚገባው በታች ከተቆረጠበት፤ የታክስ ባለእዳ ይሆናል፤ ስለዚ የጎደለውን ታክስ መክፈል ይኖርበታል። በሌላ አነጋገር፤ አብዛኛው ሰው ተመላሽ የሚያገኘው የራሱን ገንዘብ ነው እንጂ መንግስት ከካዝናው (ከራሱ) የሚመልሰው ገንዝብ አይደለም። እዚህ ላይ መስተዋል ያለበት አንድ ነገር አለ። እያንዳንዱ ተጠቃሚ፤ ከደሞዙ ላይ በቂ የገቢ ታክስ መቆረጡን የማረጋገጥ ሃላፊነት አለበት፤ በዓመቱ መጨረሻ ሂሳብ ሲወራረድ፤ እዳው ከፍ ካለ፤ ቅጣት ሊኖርው ይችላልና።

መንግስት ከራሱ ካዝና፤ ገንዘብ የሚመለስላቸው ተጠቃሚዎች አሉ። በብዛት ጎልቶ የሚታወቀው Eraned Income Credit ተብሎ የሚታወቀው ነው። ይህም ማለት፤ ሰርተው ገቢ ላላቸው፤ ገቢያቸው ግን ከተወሰነ የገቢ ወለል በታች ለሆኑ ተጠቃሚዎች ከመንግስት ካዝና የሚሰጥ ተመላሽ ነው። ከዓመታት በፊት፤ ላጤዎች የእዚህ ክሬዲት ተጠቃሚ አልነበሩም። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ላጤዎች የዚህ ከሬዲት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል። ይህ ጥቅም እንደገቢው ማነስና መብዛት የሚወጣና የሚወርድ ነው፤ መጠኑም በየዓመቱ ይቀያየራል። ለምሳሌ ለ2015 ታክስ ዘመን ላጤዎች ሊያገኙት የሚችሉት ከሬዲት ከ$2.00-$496.00 ይደርሳል። የዚህ ከሬዲት ተጠቃሚ የሚሆን ላጤ ገቢው ከ$14,950.00 በታች መሆን ነበረበት። ያገቡ ግን ልጅ የሌላቸው ደጎም የዚህ ክሬዲት ተጠቃሚ ለመሆን ገቢያቸው ከ$20,020.00 በታች መሆን ነበረበት። መመዘኛውን የሚያሟሉ አንድ ልጅ ላላቸው ገቢያቸው ከ $38,511.00 በታች ለነበረ ከሬዲቱ ከ$9.00 እስከ $3,305.00 ነበር። ሁለት ልጅ ኖሯቸው ገቢያቸው ከ $43,756.00 በታች ለሆነ ደግሞ ከሬዲቱ $10.00 እስከ $5,460 የነበር ሲሆን፤ ሶስት ልጆች ኖሯቸው ገቢያቸው ከ46,997.00 በታች ለነበረ ከሬዲቱ ከ $11.00 እስከ $6,143.00 ነበር። ይህ በ2015 ፌደራል መንግስቱ የሰጠው ከሬዲት ነበር፤ እንደየስቴቱ ደግሞ፤ ፌደራል መንግስት ከሚሰጠው ክሬዲት የተወሰነውን ይሰጣሉ። ከሬዲት ከማይሰጡት ስቴቶች መካከል ቨርጂንያ አንድ ነው። ሜሪላንድ 50% ፌደራል መንግስት የሚሰጠውን ሲሰጥ፤ ዋሽንግተን ዲሲ ደግሞ የፌደራሉን ክሬዲት 40% ይሰጣል።  ከሶስት በላይ ልጆች ላላቸው ተጨማሪ Eraned Income Credit የለም።

በተደጋጋሚ ያስተዋልኩት ነገር፤ Eraned Income Credit የሚያገኙ በዙ ሰዎች፤ ይህ ክሬዲት ከደሞዛቸው ከተቆረጥባቸው ገንዘብ ጋር የሚደመር መሆኑን አለመገንዘባቸውንና፤ የታክስ እዳም ካለባቸው፤ መንግስት ከዚሁ ክሬዲት ቆርጦ እንድሚያስቀርባቸው ያለመገንዘባቸውን ነው። ለምሳሌ፤ ሁለት ተመሳሳይ ገቢ ኖሯቸው ሁለቱም አንድ ፤ አንድ ልጅ ያላቸው ሰዎች፤ የEraned Income Credit፤ ከሬዲታቸው እኩል ቢሆንም ተመላሻቸው ተመሳሳይ ላይሆን ይችላል፤ ይህን የሚወስነው፤ ከደሞዛቸው የተቆረጠባቸው የታክስ ልክ ነው። በነገሬ ላይ ላጤዎች Eraned Income Credit ለማግኘት እድሜያቸው ከ25 ዓመት በላይ መሆን አለበት።

ለዛሬ፤ ተመላሽንና፤ Eraned Income Creditን በተመለከተ ይህን ያክል ካልኩ ፤ በዙ ሰዎችን ችግር ውስጥ እየከተተ ስላለው ስለ Itemized deduction ለዛሬ በትንሹ ለበልና፤ በሚቀጥለው ጽሁፌ በሰፊው እመጣበታለሁ፤ ለጊዜው Itemized deduction ምንድነው የሚለውን ላብራራ። የፌደራል መንግስት ታክስ ከፋዩ በሁለት ዓይነት መንገድ የሚከፍለውን ታክስ እንዲቀንስለት አማራጭ ይሰጠዋል፤ ታክሰ ከፋዩ ከሁለቱ አንዱን ዘዴ ተጠቅሞ ታከሱ አነስተኛ እንዲሆን ያደርጋል፤ እነዚህም ዘዎዴች “Itemized deduction” እና “Standard deduction” ይባላሉ፤ Standard deduction፤ ልክ እንደስሙ ለሁሉም፤ ተመሳሳይ ለሆኑ ታክስ ከፋዮች ተመሳሳይ የሆነ የገንዘብ መጠን ከገቢያቸው ላይ እንዲቀንሱ የሚፈቅድ ዘዴ ነው። ይህም በየዓመቱ የሚጨምር ነው። ለምሳሌ፤ ለ2015 የታክስ ዘመን፤ ላጤ ለሆኑ ሰዎች ሁሉ (እድሜያቸው ለጡረታ ያልደረሰ ሲሆን) Standard deduction መጠኑ፤ ወይም ከገቢያቸው ላይ መንግስት ታክስ እንዳይከፍሉብት የሚፈቅድላቸው የገንዘብ መጠን $6,300.00፤ ላገቡ ደግሞ $12,600፤ የሚያስተዳድሩት ሰው በስራቸው ላላቸው ታክስ ከፋዮች ደግሞ $9,250.00 ነበር።  “እኔ ያለኝ ወጭ ከStandard deduction ይበልጣል” ለሚሉ ታክስ ከፋዮች፤ Itemized deduction መጠቀም ይችላሉ።  Itemized deduction ሲባል፤ በመንግስት ተቀባይነት ያላቸውን ወጭዎች መደመርና ከገቢ ላይ እነዚህን ወጭዎች መቀነስ ማለት ነው። ወጭ ሲባል ግን፤ ወጪ ሁሉ ይካተታል ማለት አይደለም። በዙ ሰው ችግር ውስጥ የሚገባው፤ እነዚህን “መመዘኛ የሚያሟሉ” ወጭዎችን በተገቢ በመክተትና በመደመር ላይ ነው። በነገሬ ላይ፤ በዛው የታክስ ዘመን የሚቆረጠው የስቴት ታክስ፤ ወጭ ተብሎ ከሚደምሩት ውስጥ ነው። ለምሳሌ፤ $5,000.00 በስቴት ታክስ የተቆረጠበት ላጤ ሰው፤ $2,000.00 ያክል ለበጎ አድራጎት ድርጅት ስጥቶ ከሆነ፤ ከ6,300.00 (Standard deduction ) ይልቅ 7,000.00 (5,000 + 2,000) Itemized deduction ቢጠቀም ይመረጣል።

በዙ ተቀጥረው የሚሰሩ፤ መካከለኛ ገቢ ያላቸው፤ አንድ ስራ ብቻ የሚሰሩ ሰዎች፤ ስራቸው ከመንዳት ጋር ወይም መጓጓዣ ከመጠቀም ጋር ያልተያያዘ ከሆነ፤ ለትራንስፖርት ብለው ወጭ መቀነስ አይችሉም። ሥራቸው ከመንዳት ጋር የተያያዘ ሆኖ፤ ወይም ከስራ ጋር በተያያዘ ለመጉጓዣ ካወጡ፤ መስርያቤታቸው ለመንዳት የሚያወጡትን ሆነ የመጓጓዣ ወጭውን ከሸፈነላቸው፤ የትራንስፖርት (መጓጓዣ) ወጭ ብለው ከታክስ መቀነስ አይችሉም። በጥቅሉ፤ ከቤት ወደ ሥራ፤ ወይም ከሥራ ወደ ቤት የምናወጣው የመጓጓዣ ወጭ ለታክስ ተቀናሽ አይደለም። ስለዚህ የመጓጓዣ ወጭ ታክሳችንን ለመቀነስ ብለን ስንጠቀም በጣም ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባናል። ከዚህ በተጨማሪ፤ ለዩኒፎርም፤ ለተንቀሳቃሽ ስልክ ወዘተ፤ መመዘኛ የማያሟሉ ወጭዎች በመጠቀም፤ የታክስ እዳን ለመቀነስ፤ ወይም ተመላሽ ለማገኘትና ተመላሹን ከፍ ለማደረግ፤ የሚሰራ የታክስ አሰራር፤ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። ለታክስ እንደ ወጪ የሚቆጠሩት ምን እንደሆኑና፤ መደረግ የሌለባቸውን ነገሮች አስመልክቶ በሚቀጥለው መጣጥፍ እመለስበታለሁ። በተለይም፤ እንደ ታክሲ ባሉ በግል ሰራ የሚተዳደሩ ተጠቃሚዎች ታክስን በተመለከት ምን ማድረግ እንዳለባቸው፤ በመጣጥፌ ጠቆም አደርጋለሁ፡ እሰከዛው ደህና ቆዩ።