ከዚህ ወዴት? (በአገሬ አዲስ)

ከዚህ ወዴት?

(በአገሬ አዲስ)

የኢትዮጵያ ሕዝብ እረጅም የመከራ ጉዞ ተጉዞ አሁን ካለበት ጣምራ መንገድ ላይ ደርሷል።ጣምራ መንገዱ ወደ ተሻለ አቅጣጫ አለያም ወደ ጥፋት የሚመራ መንገድ ነው።ወደ ተሻለው አቅጣጫ የሚወስደውን መንገድ የሚመርጡት ባለፉት ጊዜያቶች ለደረሰው መከራና ግፍ፣ ለድህነት፣ለስደት፣ለእርስበርስ ግጭትና አለመግባባት፣ለአገሪቱ አለመረጋጋትና ለሕዝቡ ሰላም የለሽ ኑሮ የዳረገውን በቋንቋና በክልል ተዋረድ አዋቅሮ ሕዝብን ያለያዬ ፣ የጋራ እሴቱንና ሰንደቅ ዓላማውን ቀዶ በሌላ የለወጠ፣ሕዝብ የሚግባባበትን ቋንቋ ሽሮ በተለያዩ ቋንቋዎች እያወራ እንዳይግባባ ያደረገ፣የአገርን አንድነት ንዶ ለመበጣጠስ በመቀመር በስልጣን ላይ የተቀመጠውን አገር አጥፊ ቡድን ለማሶገድ፣ በእኩልነትና በነጻነት አንድ ሰንደቅ ዓላማ ተሸክመው የሚጓዙበት ጎዳና አንዱ ነው። በሌላው አቅጣጫ ደግሞ ያለውን አጥፊና በታታኝ ቡድን የተቃወሙ መስለው ለተመሳሳይ የጎሳ ተኮር ስርዓት የሚታገሉ፣በቋንቋና በክልል የሚያምኑ፣በአንድ ሰንደቅ ዓላማ ስር ሳይሆን እንታገለዋለን የሚሉት ጎሰኛ መንግሥት ሰፍቶ በሰጣቸው በተለያየ ባንዲራ ስር የራሳችን መንግሥትና አገር የነበረን ወይም እንዲኖረን ብለው የሚያምኑና ለማሳመንም የሚሞክሩ ፣እራሳቸውን ከሌላው ወገናቸው ነጥለው፣ታሪክና ትውልድ የሚመሰክረውን አንድነትና ውህደት ክደው ህብረተሰባቸውን ለውጭ አገር ወራሪ ሰለባና ለመከራ አጋልጠው ለመስጠት የተዘጋጁ የሚከተሉት የጥፋት መንገድ ነው። ያሉት ሁለት መንገዶች ግልጽ ከሆኑ ዘንዳ የሚያዋጣውን መንገድ የመምረጡ ውሳኔ የየአንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሃላፊነት ይሆናል። ሁሉም ተቃዋሚ ነኝ ባይ ለአገሪቱ የተሻለ ለውጥ ያመጣል ማለት ከየዋህነትም በላይ ጅልነት መሆኑን ያለፈው ታሪካችን ያስተምረናል።በደርግ አገዛዝ ላይ ከተነሱት ተቃዋሚዎች መካከል የተሳካላቸውና አሁን በሥልጣን ኮርቻ ላይ የተቀመጡት የጎሳ ቡድኖች ያመጡትን ውጤት በማየት የዛሬዎቹ ተቃዋሚዎች መካከል በተመሳሳይ መልክ በጎሳ የተደራጁት ቡድኖች በውጭ አገር ሃይል እርዳታና ግፊት ተሳክቶላቸው ስልጣኑን ቢይዙ እንኳን ምን ለውጥ ሊያመጡ እንደሚችሉ ከአነሳሳቸውና ከሚከተሉት መንገድ ማወቅ ይቻላል።የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዳግመኛ ጊዜ በጎሳ ስብስብ ቡድኖች ላለመገዛት እንደቆረጠ ብዙ ምልክት እየታዩ ነው።በብሔር ነጻነት ስም የሚመጣ የመገንጠል ውጤቱ ህዝቡ ቋንቋውን በሚናገሩ አምባገነኖች መዳፍ ስር መውደቅና በራሱ አባዱላዎች እየተቀጠቀጠ የሚኖርበት አዲስ የመከራ ምዕራፍ መክፈት ማለት ነው። በአጭሩ ሲገለጽ ለውጡ የጅራፍና የገራፊ ለውጥ ነው።እሩቅ ሳይኬድ ኤርትራን ያዬ ልገንጠል አይልም።ያንን ማስተጋባት ድክመት ብቻ ሳይሆን ለራስና ለልጅ ልጅ የሚተርፍ ሃፍረትና የታሪክ ቁስል አስቀምጦ ማለፍ ይሆናል። በጎሳና በቋንቋ እምነት ይንቀሳቀሱ የነበሩት ቡድኖች ደርግን ጥለው ያመጡት ለውጥ ቢኖር አሁን የምናየውን የመበታተንና የእልቂት፣የዘረፋ ስርዓት ነው፡፤ጨፍጫፊውን የደርግ ስርዓት ጥለው የተሻለ ሰላም አላሰፈኑም። ሕዝቡንም ከመሞት፣ከመቁሰል፣ከእስራት፣ከስደት አላዳኑትም፤ በበለጠ ደረጃ የነዚህ ሁሉ ሰለባ አደረጉት እንጂ። በተጨማሪም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በመንግሥት ደረጃ በከፍተኛ መጠን ያልታዬ ሌብነት፣ዘረፋ፣ሙስና የተካሄደው በዚህ ተቃዋሚ ነኝ፣የተሻለ ስርዓት አመጣለሁ ብሎ ስልጣን ላይ በወጣው የጎሳ ስብስብ ቡድን ወቅት ነው።ወደፊትስ ሕዝብ ያልመረጣቸው በዚሁ መልክ የተደራጁ የጎሳ ቡድኖች ከአንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በሃይል ወይም በውጭ እርዳታ የስልጣኑ ባለቤት ቢሆኑ ዋስትናው ምን ያህል ነው?አሁን በአንዳንድ ቦታዎች በሚደረጉ ሰላማዊ ሰልፎችና ንግግሮች የመስማማት ሂደቶች እንደተደረጉ ይነገራሉ፤ ይታያሉም፤ግን ለአንድነት ማረጋገጫ በሆነው በአንድ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ፣አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ስር ሲሰለፉ አይታዩም። አልፎአልፎም ተነጥሎ የራስን ሰላማዊ ሰልፍ በራስ ባንዲራ ስር ሲካሄድ ተስተውሏል።እንደነበረው የኛና የናንተ በሚለው ልማድ ተቀጥሎበታል።ጣዲያ አንድነቱ እምኑ ላይ ነው?አሁን የሚታየው መቀራረብ ለወደፊቱ ዋስትና ቢሰጥ መልካም ነበር፣ግን የጊዜና የጉልበት መግዣ እንዳይሆን ያሰጋል።ጡንቻን ለማዳበር የሚረዳ የፑሽአፕ መሬት ላለመሆን ጥንቃቄ ማድረጉና ማረጋገጫ መያዙ ተገቢ ነው። ይህ አውሬ ህወሃት የተባለ ቡድን ስልጣኑን ከደርግ ሳይነጥቅ ገና በትግል ስም ይንቀሳቀስ በነበረበት ጊዜ ዓላማው ሳይገባን ደርግ የተባለው አውሬና ጨካኝ ቡድን በመሰረተው ስርዓት በፈጸመው ጭፍጨፋና ግፍ የተነሳ በቁጭትና ጥላቻ በመነሳት ማንም ይሁን ማንም ከደርግ ሳይሻል አይቀርም በሚል ጭምብልታ ዓላማቸውን ሳንጠይቅና ሳንረዳ፣ሳንቃወም፣ ድጋፍም ባይሆን በዝምታ አሳልፈን ለዚህ መብቃታቸውን ስናይ የሚቆጨን ብዙዎች ነን።ታሪክ እራሷን ትደግማለች እንደሚባለው አሁንም የዚያን አይነት አካሄድ እየተከሰተ ይታያል። ወያኔን እንቃወማለን ግን በኢትዮጵያዊነት አናምንም፣ የተለየ የራሳችን ባንዲራና ቋንቋ፣ባህልና ታሪክ ያለን፣በኢትዮጵያውያኖች ተወረን የተያዝን ለነጻነት የምንታገል የቅኝ አገር ሕዝቦች ነን ብለው ኢትዮጵያን ለመቀራመት ሳንጃ ስለው የወጡትን የተለያዩ ቡድኖች፣ዓላማና ስማቸውን ሳይቀይሩ ለዴሞክራሲ የሚታገሉ ናቸው ብሎ የአገሩን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በእነዚህ ቡድኖች ባንዲራ ተክቶ ወይም ጎን ለጎን ተሸክሞ ሕዝቡን በማማለል በብዥታ ዓለም ውስጥ የሚከንፈው ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለው ወገን እረጋ ብሎ በሰከነ መንፈስ የሚያደርገውን በማስተዋል፣ነገ ሊያመጣ የሚችለውን ውጤት ሊያብሰለስለው ይገባዋል።በራስ መተማመን ማለት ሳያወላውል ኢትዮጵያዊነቱን በሰንደቅ ዓላማው ሲያስመሰክርና ሲኮራበት ነው።ለሌሎች መብትና እኩልነት መታገል ማለት እራስን መስዋእት አድርጎና አዋርዶ የሌሎችን የጠባብነት ፍላጎት ተቀብሎ ማጫፈርና ማስተጋባት ማለት አይደለም። ኢትዮጵያዊነትና የኢትዮጵያን አንድነት ማስከበር ማለት ለመገነጣጠል የተለየሁ ነኝ ብሎ ባንዲራ ሰፍቶ የሚንቀሳቀሰውን ማጀብና ማበረታታት የነሱም መሰላል መሆን አይደለም።ወይም በጮሌነት በእዚያ የጎሳዎች ግርግር ጀርባ ስልጣን ላይ እወጣለሁ ብሎ ለሚያስብ ግለኛ ቡድን መሳሪያ መሆን ማለት አይደለም።ይህ አሁን በስልጣን ላይ ካለው አጥፊና በታታኝ ቡድን ከተከተለውና ከሚከተለው አካሄድ የተለዬ አይደለም።በዚያ መንገድ ከቀጠለ ጉልቻ ቢለወጥ እንደሚባለው ነው።ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከእሳት ወደ ረመጥ ወይም ከድጡ ወደማጡ መግባት ይሆናል።የአራዳው ፖለቲከኛ ተቆርቋሪ መስሎ ጎሰኞችን በማሰባሰብ ብሎለት ለሥልጣን ቢበቃ በማግስቱ “ሲያምራችሁ ይቅር” ብሎ ሊሸውዳቸው ይችላል፤ያ ከሆነ ደግሞ ቀውሱ በቀጣይነት ይኖራል ማለት ነው።ስለሆነም በቁርጠኝነት በኢትዮጵያ ውስጥ ዳግም የጎሳ ስብስብ የሚቆጣጠረው መንግስት እንዳይመጣ፣የአገሪቱን መከፋፈልና መገነጣጠል በአዋጅ የሚያጸድቀው አንቀጽ ሰላሳ ዘጠኝን የሚያስተናግዱ ሃይሎች ፍላጎት እንዳይሰምር የሚሻ ሁሉ በአንድነት ቆሞ ለውጭ አገር መንግሥታት ጥቅም በሚያመቸው መንገድ የሚበጠበጠውን ጥንስስ መርዝ ላለመጋት የአገሩን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርጎ በአደባባይ ደረቱን ነፍቶ መጮህ ይገባዋል።ይህ አንቀጽ ሰላሳዘጠኝ ኢትዮጵያን ባለቤት የሌላት የኪራይ ቤት የሚያደርጋት፣ የሚያድሳት ሳይሆን የሚያፈርሳት፤ሕዝቡንም የአገሩ ባለቤት ሳይሆን ተከራይ አድርጎ በፈለገበት ጊዜ በነጻነት ስም ለቆ ሊወጣ የሚያስችል፤በፈለገበት ያገሪቱ መሬት እየኖረ ሰርቶ የመኖርን መብት የሚገፍና በጠባብ መሬት ከርችሞ የሚያስቀር ፤ብሎም በወሰንና በክልል ምክንያት ኑዋሪውን ሲያናቁርና ሲያጋጭ የሚኖር ሕግና አንቀጽ በመሆኑ መወገዝና መሰረዝ ይኖርበታል። በዚሁ አንቀጽ አማካይነት አሁን አገሪቱን ቋንቋን መሰረት ባደረገ በፌዴራሊዝም ስም የክልል አስተዳደር መሸንሸኑ ያመጣው ጥቅም ሳይሆን የመገነጣጠልን አደጋ የሚያስከትል ነው።ስለሆነም በዚያ መልክ መቀጠል ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። አሁን ያለው ቋንቋንና ጎሳን መሰረት ያደረገ የክልል የመንግሥት አወቃቀር ተወግዶ አገሪቱ በአምስት ማለትም ሰሜን ኢትዮጵያ፣ደቡብ ኢትዮ፣ምስራቅ ኢትዮ፣ምዕራብ ኢትዮ.እና መሃል ኢትዮ.በሚል የአስተዳደር ክፍሎች ቢከፋፈል ወይም እንደቀድሞው በክፍለሃገሮች መልክ ቢዋቀርና የየራሱ የሕዝብ ምክርቤቶች ከቀበሌና ወረዳ ጀምሮ ቢኖሩት በአገር ደረጃም ከሁሉም የተውጣጣ ብሔራዊ ም/ቤት ቢኖረው ከአሁኑ አደገኛ አደረጃጀት የተሻለ ይሆናል። በምክርቤቶቹም ሆነ በመንግሥት ስልጣን ላይ የሚቀመጡት በጎሳቸው ሳይሆን ከጎሳና ከሃይማኖት ነጻ የሆነ በፖለቲካ መስመራቸው፣በሚያወጡትና በሚከተሉት መመሪያ ቢሆን ከሰለጠነው ዓለም አሰራር ጋር ይጣጣማል። ሕዝቡም በጎሳው ሳይሆን እንደሰው በአስተሳሰብ እረድፍ ተሰልፎ በፖለቲካ ብስለት ለእድገትና ለመሻሻል የሚመካከርበትና የሚወዳደርበት ዕድል ይቀዳጃል።የከባቢ አስተዳደሮች የሚተሳሰሩበትና የሚተዳደሩበት በሕዝብ ተሳትፎና ፈቃድ የረቀቀ አንድ ብሔራዊ ሕገመንግሥትና በሕዝቡም ነጻ ምርጫ አንድ ማእከላዊ መንግሥትም መኖሩ የአሁኖቹን ቋንቋ ተኮር የክልል መንግሥታትና አደጋውን ሊያሶግድ ይችላል። ኢትዮጵያ ስንል የአንድ ቋንቋ፣የአንድ ባህል የአንድ እምነት ብቻ የሰፈረባት አገር ማለት አይደለም።ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ የሚያሰኛት የልዩልዩ ባህል፣ቋንቋ፣እምነት፣መልክና መልክዓምድርን አቀናብሮ የያዘ ሕዝብ የሚኖርባት አገር በመሆኗ ነው።በዚህም መልክ ወራሪ ጠላቶቿን መክታ ለብዙ ዘመናት በነጻነት ለመኖር ችላለች። አሁን የኢትዮጵያ ሕዝብ በመስቀለኛ መንገድ ላይ ቆሟል ሲባል ከላይ በተጠቀሱት ሰልፎች ማለትም የአንድነት ሃይሎች ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን የሚያንጸባርቀውን አንድ ሰንደቅ ዓላማ ፣አረንጓዴ ቢጫና ቀይ አንግበው የጎሳ ፖለቲካ ባፍንጫችን ይውጣ፣እምቢኝ ዳግመኛ ብለው የተሰለፉበት ገንቢ መንገድ ሲሆን በጎሳና በክልል ተሸንሽኖ በአማራነት፣በኦሮሞነት፣በትግሬነት፣በአፋርነት፣በሲዳማነት፣በጉራጌነት፣በኦጋዴነት፣በቤኒሻንጉልነት፣በአኝዋክነት፣በጋምቤላ ነት…ወዘተ የተለያየ ባንዲራ ሰፍተው የተሰለፉበት ሌላው የጥፋት፣ሌላው የዳግማዊ ህወሃት መንገድ ነው። ምርጫችን አንድ ሊሆን ይገባል፡፤መጥፋትን፣መለያየትን፣ቀውስን፣የማንፈልግ ከሆነ በሚያስተባብረን በኢትዮጵያዊነት መንፈስና በአንድ ሰንደቅ ዓላማ ስር መሰለፍ አለብን።ዛሬ የተለያዩ ባንዲራዎችን ማስተናገድ ማለት ነገ ነጻ ለመውጣት የሚሹትን ተገንጣዮች ማበረታታትና እውቅና እንዲያገኙ፣ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትም እንዲያከትም ማድረግ ነው።ለኢትዮጵያም ብቻ ሳይሆን ለሌላው ያፍሪካ ሕዝብ መበታተንና የእርስ በርስ እልቂት የጥፋት ደወል መደወል ማለት ነው።ባንዲራ ከመሸከማችን በፊት ትርጉሙን ማወቅ ይገባናል።ባንዲራ የሚለው ቃል እራሱ ከጣሊያኖች የተወረሰ ነው።የእኛ የነጻነት አርማችን ሰንደቅ ዓላማ ነው።እሱም የነጻ አገርና ሕዝብ መለያ መሆኑን ልንገነዘበው ይገባል።ሰንደቅ ዓላማ የአገርን ዳርድንበር የሚያረጋግጥ ምልክት ነው።አሁን በአገራችን በልዩ ልዩ ጎሳዎች ስም ባንዲራ ሰፍተው የሚታገሉትን የመጨረሻ ፍላጎታቸውን ብንመረምር ወደጥፋት የሚወስድ እንደሆነ አይካድም።ታዲያ የነሱን ባንዲራ ማውለብለብ ወይም ሲያውለበልቡ ማጀብ ፍላጎታቸውን መቀበልና ማጽደቅ ነው።ኢትዮጵያ አንድነቷ ተናግቶ በተለያዩ ትናንሽ መንግሥታት ተቀይራ በማያቋርጥ ጦርነት ውስጥ ትኑር ማለት ነው።ለኢትዮጵያም ሆነ ለኢትዮጵያኖች የሚያጠፋቸው እንጂ የሚጠቅም አመለካከትና አካሄድ አይደለም። በአገራችን በኢትዮጵያ ለሚኖረው ሕዝብ አንድነትና እኩልነት መቆም ማለት ሁሉም ኢትዮጵያዊ በደምና በአጥንቱ አስከብሮ የኖረውን ሰንደቅ ዓላማ በሌላ መለወጥ አይደለም።ስለሆነም በአደባባይ ሰልፋችንና የጋራ በዓላችን ላይ አንድ ሰንደቅ ዓላማ ይዘን እንውጣ።የአንድ አገር ዜግነታችንን እናረጋግጥ። በተደጋጋሚ እንደታየውና አሁንም እንደሚታየው በተሳሳተው መንገድ ውስጥ ገብተው የሚዋዥቁት ኢትዮጵያውያን ቁጥራቸው እየበዛ መጥቷል።ከጋረዳቸው ብዥታ ወጥተው ብዙ ባንዲራ አሸክሞ የሚያሰልፋቸውን፣ የሚደግፉትን ድርጅት ሊጠይቁትና ከሰመጠበት አዘቅት ጎትተው ሊያወጡት ይገባል።ጭፍን ድጋፍ መስጠት የሚከተሉትና የሚደግፉት ድርጅት ገደል እንዲገባ መግፋት፣አገርንም ለዳግመኛ ጥፋት አሳልፎ መስጠት ስለሚሆን በኢትዮጵያዊነትና በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ስር ብቻ የሚደረገውን ሕዝባዊ ትግልና እንቅስቃሴ ሲሆን እንዲቀላቀሉ አለያም ከመጥለፍና መልኩንና መልእክቱን ወደሌላ አቅጣጫ እንዲቀለበስ ከማድረግ እንዲታቀቡ በወገናዊነት ምክር በቃችሁ ሊባሉ ይገባል።የተለያየ ባንዲራ መሸከም ማለት የሌሎቹን ወገኖቹን ሰብአዊ መብታቸውን ማክበር ማለት አይደለም። መቃወምም ማለት የዜጎችን እኩልነትና መብት መቃረን ማለት አይደለም።በአንድ ሰንደቅ ዓላማ ስር እንዲሰለፉ ማድረግ በእኩልነት እንዳይለያዩ በሚያስተሳስር የጋራ ገመድ መሰብሰብ ማለት ነው።የተለያዩ ባንዲራዎችን መቃወም ማለት መለያየትንና ለእርስ በርስ እልቂት የሚያበቃውን የልዩነት መንገድና በር መዝጋት ማለት ነው። በሌላም አቅጣጫ በንግግርና በአገላለጽ ትልቅ ስህተት እየተሰራ መሆኑን ማጤን ያስፈልጋል፤ይኸውም የኢትዮጵያና የኦሮሞ፣የኢትዮጵያና የኦጋዴን፣የኢትዮጵያና…ወዘተ ኮሚኒቲ ወይም ስብስብ የሚሉት አገላለጾች ሌላውን ከኢትዮጵያ ጎራ የሚያሶጣና የሚያራርቅ፣የሚነጣጥል አገላለጽ ስለሆነ መታረም ይኖርበታል።ይህ ካልሆነ እንደ ሰንደቅ ዓላማው ብዛት ልዩነትን ማስተናገድ ይሆናል።ኢትዮጵያዊ የሚለው የወል አጠራርና ስያሜ የሁሉም እንጂ የአንድ ጎሳ መለያ መጠሪያ አይደለም። ለድል የሚያበቃው መንገድ በኢትዮጵያዊነት የሚያምነው ሁሉ፣የድርጅት አባዜውን ጥሎ አገር አድን በሆነው ትግል ውስጥ የጋራ አመራር መስርቶ መታገል ብቻ ነው።በመቀጣጠል ላይ ያለውን ሕዝባዊ ትግል እየረዱና ምክር እየሰጡ አገሩን ከተገንጣዩችና ከወያኔ ሴራ የማዳኑ ተግባር ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል።አገር ከዳነ በዃላ ለሚመሰረተው የሽግግር መንግሥት አሁን በትግሉ ሂደት ውስጥ እያለ የሽግግር መንግሥቱን እርሾ ሊጥል ይችላል።ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ እንዳይሆን አሁን ተቀራርቦ መነጋገርና መመሪያውን መንደፍ ይኖርበታል። ተባብረን አገራችንን እናድን!!ከዘገዬ በዃላ መሯሯጡ ጥቅም የለውም።

አገሬ አዲስ