ወያኔን ኢንቡልኑ። (በዳዊት ዳባ)

ወያኔን ኢንቡልኑ።

አገሬው በሺዎች ልጆቹን እየቀበረ፤ በአስር ሺዎች ወደማጎርያ እየተጋዘ። በሚሊዬኖች አደባባይ ወጥቶ እየታገለ ነው። አሁን ላይ መሸፋፋኛው ተገላልጦ ፍንትው ብሎ የወጣው ታላቁ የህዘብ ጥያቄ “ የህዋዋት የበላይነት በቃ” የሚለው ነው። ይህ ማለት “የስርአት ለውጥ ነው”። ህዘብ በቃ ሲል በጠቅላላ በአገሪቷ ላይ ካሰፈኑት ፈፁም የበላይነት በተጨማሪም ኢህአዲግ በሚለው ስብስብ ውስጥ ያለው የበላይነትና አድሏዊነት ይብቃም እያለ ነው። ይህ ድምፅ ከውጪ ብቻ አይደለም እየተሰማ ያለው። እዛው ከውስጣቸውም እያየለ እየመጣ ነው። አዎ የደርግን ስርአት በጦርነት አሸንፋዋል። አሸናፊነት የሚሰጠውን ሁለንተናዊ ጉልበት ውስን ለሆኑ አመታት በተለየና በነበረው ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ ለሚዛኑ መዛባት ምክንያት አድርጎ መውሰድ ይቻል ይሆናል። ይህም እንኳ ለከት ባለው ሁኔታ ተደርጎ ቢሆን ኖሮ ነው። ለኦሮሞዎች ድርጅት እንፍጠር ብለው ከምርኮኞች ሰርተዋል። ለአማራዎች ድርጅት እንፍጠር ብለው ደግሞ እንዲሁ ፈጥረዋል። እንዲህ እንዲህ እያሉ ለሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ድርጅቶች ፈጠሩ። እነዚህ ድርጅቶች በሰዎች ነው የተሰሩት። እንዳሻቸው ጢቢ ጢቢ እንዲጫወቱባቸውና ለሀያ አምስት አመት መጠቀሚያ ሊያደርጓቸው መቻላቸው የሚሰግርም ነው። ያም ሆኖ የፈለገውን አይነት ክትትል ግምገማና ጥቅም ይኑር። ቋንጃቸው አልተሰነኮለም። አንገታቸው ላይ ሰንሰለት አልታሰረም። ሁሌ መሳርያ የያዘ አካል ማማ ላይ ቆሞ አይጠብቃቸውም። ይህም ተደርጎ ቢሆንም እንኳ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ የትግሬ ወያኔዎች አገዛዝ ፍፃሜ ላይ ይህ ክፍል የሚኖረው ትልቅ ሚና ቀድሞ ማየት መቻል አለመቻል ካልሆነ ሳይታለም የተፈታ ነበር። እነዚህ ድርጅቶች ውስጥ ድርሻ ያደረጉ ከላነሰ ምን አልባትም ከተሻለ ማህበረሰባዊ እሴት ካለው ህዘብ ውስጥ የወጡ ናቸው። የበዙት በእድሜያቸውማ ሆነ በጉልበታቸው ካሳዳሪዎቻቸው የበረቱ ናቸው። በአይምሮም ሆነ በመማር ካገኙት እውቀትም በልጠዋቸዋል። በቁጥር አጥፈዋል። በድርጅት ጥንካሬም እንዲሁ። በአግባቡ አልተጠቀሙበትም እንጂ ከወከሉት ማህረሰብ ብዛት አኳያ ሊሰጣቸው የሚችለው ጉልበትም የትየለሌ ነበር። እርቀን ካለነው በተሻል በቅርብ ሆነው ብልግና ቆሞ ሲሄድ አይተዋል። ወገንታዊነት ሊኖራቸው አይችልም አያማቸውም ብሎ ማሰብ የአቦይ ስበሀት ድንቁርና ብቻ ነው። ዛሬ የምናየው የነዚህ ጉዳዬች ድምር ውጤትን ነው። ከአመት በፊት ኦፒዲዬዎች የተመከሩት ህወሀት እራሱን ችሎ የኦሮሞን ህዘብ አፍኖ ሊገዛ በጭራሽ አይችልም። የታፈነ የኦሮሞ ህዘብ ማለት ጢቢ ጢቢ መጫወቻ ስትሆኑ መኖር ነው። ሊገባችሁ ከቻል ቀላሉ መንገድ ህዝቡን ልቀቁት ነበር። ከምትግመቱት በላይ ጉልበት ይሆናችሗል ነበር። ይህ በሌሎች አጋር ድርጅቶች ዘንድ የተወሰደ ተሞክሮ ነው። ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ አነድ ጊዜ ላይ ቀለል አድርገው አመላካችና የምታድግ ግን የማትመስል አሳብ ጣል አድርገዋል። “እንቢ ካሉ ሌሎቹ እራሳቸውን ችለው መንግስት መሆን ይችላሉ” የምትል። መሳርያ የያዘው ላይ በመለጠፍ መትረፍ ይቻላል የሚለውም ህልም ነው። ጉዞው የሗልዬሽ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ጀነራሎቹ እንጂ አብዛኛው ሰራዊት የናንተ አይደለም። ህዘብ ነው። የደሀ እናት ልጆች ናቸው። የወገኖቹ ደም በመላው አገሪቱ የሚንዥረዥር። ለራሱም ያልተመቸው። ጠቀላላ የአገሩና የወገኑ ሁኔታ የሚያመው። አዎ ቁጭ ብሎ የመምከር አማራጮችን የማየት በአጠቃላይ ትግሉን በጋራ ለማድረግ በአፈናው ምክንያት ክፍተቶች አሉበት። የማይሞሉ ወይ ሊሞላቸው የማይቻለው ግን አይደሉም። ፈዛዛ ተቃዋሚ መኖሩ ነው እንጂ ድሮ በቀላሉ ሊሞላ የሚችል ነበር። አሁንም ቢሆን ሌላው ቀርቶ የጊዜ፤ አጋጣሚና ቦታ መመቻቸት በራሱ ደህና ሁኑን ለሁሌው ሊያመጣ ይችላል። ይህ የህዘብ ትግል በሁሉም አገሪቷ ክፍል ባንድ ጊዜና ሰዓት በአገር አቀፍ ደረጃ መደረጉ አይቀርም። የዚህ አይነት ሁኔታዎች ከዛሬ ጀምሮ ሁላችንም ነፃ ነን የሚለውን መናበብና ስሜት መፍጠሩ አይቀርም። የአገሪቷ ጠቅላላ ሁኔታ የሚሻውም ይህንኑ ነው። የኦሮሞ ተቃውሞ ጥንካሬ አንዱ መገለጫ ስርአቱ ውስጥ ያሉ ወገኖቻቸውን መዚገብ ገልጠው የለውጡ አካል የሆነውን ካልሆነው መናገር መቻላቸው ብቻ ሳይሆን ከበዙት ጋር አስፈላጊ ሲሆን ሊደርሷቸው የመቻልን አቅም መገንባታቸው ነው። በግሌ ከአመታት በፊት የኢላሞ ሞልሞሌ ቀበሌ ሊቀመንበር ስሙ ማነው? ባለቤቱስ ማን ትባላለች? የጅ ስልኩስ? ብዬ ነበር። ምን እናድርገው? ድክመት ሆኗል። አሁንም ሊሰራ የሚቻል ነው። ቀድሞ አስቦ መስራት የብልሆች ነው። አንዳንዴ ደግሞ ግድ ሲል በዘመቻ በሳምንታት ይሰራል። ሁሉን ያቀፈ ትብብር ማቆሙም እንዲሁ። ይህ ሀሳብ በዜጎች ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው መሰረቱ የተጣለ ነው። አንዳንዴ አሜሪካኖች ጠርተው ኑ እዚህች ላይ ፈርሙ እስኪሉ የሚጠበቅ ይመስላል። እውነት ለመናገር ዲሞክራሲያዊት ፤ ፍትህና እኩልነት የሰፈነባት የሁሉንም ፍላጎትና ጥያቄ ማስተናገድና ብሎም መሸከም የምትችል አገር እንዲኖረን አሁን የተፈጠረውን አይነት አጋጣሚ መቼም ተፈጥሮ አያውቅም። ከወያኔ በሗላ ጦር ሀይል ፖሊቲካው ውስጥ የለም። ደርግ ጦር ነበረው። ወያኔ ጦር ይዞ ነው የገባው። አሁን ማንም ፍላጎቱን አቻችሎና ተደራድሮ፤ በዜጎች ፍላጎት ተዳኝነቶ ካልሆነ ፍላጎቱን በጦር ሐይል መጫን የሚችልበት ሁኔታ የለም። ወያኔን ባዶ እጁን ታግሎ የጣለ ህዘብ ለትናንሽ ባለመሳርይዋች ወይ ጉልበታሞች ይገብራል መጃጃል ነው። አጉል ፍርሀትና ጥርጣሬ ካልሆነ መጪው ጊዜ ለሁሉም ብሩህ ነው። መተባበር አብሮ መታገል ሽግግሩንም መስራት ይቻላል። {የዚችን ፓራግራፍ ይዘት የያዘ አነጋገር ረፋዱ ላይ አቶ ሌንጮ ለታ ኦ.ሜ.ኔ ላይ ያደረገው ቃለ መጠይቅ ላይ ሲጠቀም ሰማው}። በነገራችን ላይ የትብብሩ ፋይዳ ለወደፊት እነሌንጮ ድርጅታዊ ጥንካሬ ሊገነቡ ከቻሉ ካልሆነ አልታየኝም። እንደውም ጊዜው ለሚሻው ትልቅ ነገር ዝም ብሎ አፍ ማዘጊያና መከፋፈያ አድርጌ ነው የወሰድኩት። ያም ሆኖ በሽግግሩ አዳልጦን ማጥ ውስጥ እነዳንገባ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። አይደለም ከፈላጭ ቆራጭ አንባገነን ወደዲሞካራሲያዊ ሁሌም ቢሆን መንግሰት መቀየር እንደተባለው ያው ዳይፐር መቀየር ነው። ሲቀይሩ ላለማነካከትም ሆነ ቶሎ ቶሎ በአዲስ ይቀየር የሚባለውም ለዚሁ ነው። መቀየሩ ጥሩ ግድም ሆኖ እያለ ያገለገለ ከቆሻሻ ውስጥ አውጥቶ አድርግ አታድርግ በሚል ግብ ግብ አገሩን በሙሉ አር እንዳናናካካውም መጠንቀቁም አይከፋም። ለፈለገ ከድል በሗላ ይህም ሀሳብ ችግር የለውም። ከድል በፊት ትግሉ ውስጥ ማስሮጥ ግን ህዘብ መራራ መሰዋትነት ከፍሎ ወደፊት ያስኬደው ትግል ላይ መከፋፈያ ታኮ ይሆናል። ምንጩ ደግሞ ይታወቃል ድክመት ነው። በመጀመርያ እናሸነፍ። ከዛ ያሉ ፖለቲካዊ ፍላጎቶችና ልዩነቶች ሰላማዊ ህጋዊና መዋቅራዊ በሆነ መንገድ እንደባደብባቸው። ጊዜው የኔን መንገድ በትንሹ። ብዙ የጋራ ስራን ግድ የሚል ነው። አገዛዙ የፈለገውን ያህል ቢዳከም ፍፃሜውን ማድረግ ብዙ ስራን ይፈልጋል። ከዛም ባጭር ጊዜ ውስጥ ሰላም መረጋጋትን ማስፈንና አልፎም ህግና ስርአት በቶሎ እንዲጠበቅ የሚያስችል ብቃት ላይ ማቀድ፤ በዝርዝር መዘጋጀትና የመተግበር ዝግጁነትን መፍጠር ደግሞ አለ። ይህን አለማድረግ እንዝላልነት ብቻ ሳይሆን አስጠያቂም ነው። በግልሰብ ደረጃ ሎተሪ ቢደርሰኝ ብሎ ከዛ ተነስቶ ማለም ወይ ማቀድ ይቻላል። በአገርና በሕዝብ ግን አንባገነን እየታገልክ ላዛውም የኛዎቹን እያወቅናቸው ፖለቲካዊ ማሻሻያ እንዲያደርጉ ሲጠብቁ መዘናጋት ሀላፊነት የጎደለው ይሆናል። ከአንዷለም ይፈታም ሆነ ፖለቲካዊ ማሻሻዬዎችን አስቀምጦ መታገያ ማድረጉ ማለፊያ ሊሆን ይችላል። ይህ አያከራክርም። ከዛ ባለፈ ሰላም የሰፈነባት የተረጋጋች ዲሞክራሲያዊ ኢትይጵያ ያለነሱ በጎ ፍቃድ አይመጣም ካልን መታገል ሳይሆን ቤተ መንግስት በር ላይ እየሄድን ምህላ መያዙ ይሻል ነበር። በዛ ላይ ልናገኝ የምንችልው ውጫው ድጋፍ ለውጡን መሸከም መቻላችን ላይ የሚታይ፤ ሊተገበር የሚችል ዝግጅት በዝርዝር አስቀምጠን ማሳመን ከመቻላችን ጋር በቀጥጣ ይገናኛል። ይሄ ሁሉ በተናጠል በሚደረግ እሩጫ ሊሰራ አይችልም። ሽግግር ግድም፤ ሀላፊነትም፤ ስራም ነው።

በዳዊት ዳባ