የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዞና የህዝባዊ አመፅ እንድምታዎች (ያሲን መ. ያሲን)

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዞና የህዝባዊ አመፅ እንድምታዎች (ያሲን መ. ያሲን)

The Current Ethiopian Political Developments and the Implications of Popular Insurgency (Yassin M.Yassin)

የኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ትኩሳት ባለፉት ሩብ ምዕተ ዓመታት በኢህአዴግ ዘመነ ግዛት ከተከሰቱ አንኳር ህዝባዊ ንቅናቄዎች ግለቱ የናረና ለስርዓቱም ቁመና ሆነ ለአገሪቱ ፖለቲካዊ የለውጥ ሂደት ቁብ ያለው ተፅዕኖ ፈጣሪ ክስተት እንደሚሆን መገመቱ ጥርጥር የለውም፡፡ በአገሪቱ ከአፋር ኩነባ እስከ ደቡብ ኮንሶ ወረዳዎች፤ በተለይም በመላው ኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በጥልቀት እየተቀጣጠለ የሚገኘው ህዝባዊ እምቢተኝነት ለወራት ጋል በረድ እያለና ቦታዎችን እየቀያየረ የቀጠለ ሲሆን በመንግስትም በኩል እንደተለመደው ጠንካራ ክንዱን ለቡጢ ከመሰንዘር አልቦዘነም፡፡ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚም ለወራት ካንቀላፋ በኋላም ቢሆን ህዝባዊ ተቃውሞን ወደ ጠረጴዛ አቅርቦ በዚያውም የድርጅቱን የ15 ዓመታት ጉዞ እንደገመገመና የችግሩን ምንጭ ነቅሶ ማውጣቱን አስረግጦ ገልጿል፡፡ የወቅቱ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ምንጭ ባለፉት 15 ዓመታት ኢህአዴግ ያስመዘገበው የኢኮኖሚ እድገት እንግዴ ልጅ መሆኑንና ጥቂት የፖለቲካ አመራሮች ስልጣናቸውን ተገን አድርገው ከተመነደገው የኢኮኖሚ እድገት እየቆነጠሩ ኪሳቸውን ማድለባቸው ህዝቡን ማስቆጣቱ አሙን መሆኑን አብስሮናል፡፡ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከቀናት ግምገማ በኋላ ደረስኩበት ያለውን የአገሪቱን የፖለቲካ ችግር ምንጭ ከማብሰሩ ጥቂት ሳምንታት ቀደም ብሎም የቀድሞ የህወሃት የአመራር አባልና የጦር መሪ የነበሩት ሌ/ጀኔራል ፃድቃን ገ/ትንሳይ ኢትዮጵያ በመንታ መንገድ ላይ መሆኗን ገልፀው የችግሩን ምንጭ ግን ብርቅየውን ህገ መንግስት በተገቢው መንገድ አለመተግበሩና በጥቅሉ ፀረ ዲሞክራሲያዊነት በኢህአዴግ ውስጥ በጥልቀት መንሰራፋቱ እንደሆነ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ድርጅቱም ሆነ የቀድሞ ታጋዬ ከቀናት ግምገማም ሆነ ከአመታት ተሞክሮና ጥናት በኋላ ደረስንበት ያሉት አገሪቷን ላጋጠማት ፖለቲካዊ ራስ ምታት ዋነኛ ምንጭ አገሪቷ ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ሲመዘን ውሃ ካለመቋጠሩም በተጨማሪ ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላን ቢያስተርት ብዙም ላያስገርም ይችላል፡፡ የአንድን ችግር ዋንኛ መንስኤ ነቅሶ ማውጣት ለመፍትሄው ግማሽ መንገድ እንደመጓዝ ይቆጠራል እንደሚባለው የአገሪቷ ወቅታዊ የፖለቲካ ራስ ምታት እንበለው ነቀርሳ ምንጩ አንድና አንድ መሆኑን አድምቆ መናገር የግድ የሚል ይመስላል፡፡ አገሪቱን በቀላሉ ለማትወጣበት የፖለቲካ አዙሪት የዳረጋት ህወሃትን የተጠናወተው ሁሉን ጠቅልል አባዜ መሆኑ አሌ የማይባል እውነታ ነው፡፡ የንጉሱን ፈረስ ስም “አባ ጠቅል”ን የመውረስ አባዜ! ይህም ችግር ከህወሃት ፅንሰት፣ ውልደትና እድገት ጋር እጅግ የተቆራኘ ግንኙነት አለው፡፡ ህወሃት ሲጸነስ እንቁላሉም ውሃ ዘሩም ከትግሬና ትግሬ ብቻ የተዳቀለ፤ ውልደቱም ከመረብ ወዲህና ከመረብ ወዲያ በታጠረ ትግሬነትን ማዕከል ባደረገ በረት ውስጥ፤ እድገቱም እንዲሁ 2 በጠባቧ የትግራይ መሬት የተገታ በመሆኑ አሁን ከምናየው ህወሃት ሌላ አይነት ህውሃት መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡ እንደዚህ አይነቱ ተክለ ቅርጽ በመያዙ ህወሃትን መውቀሱም ፋይዳ አይኖረውም ምክንያቱም ይህንን ፅንስ እስከ እድገት ደረጃ ያደረሱት ብዙ ብዙ ፖለቲካዊ ምክንያቶች መኖራቸው ጥርጥር የለውምና፡፡ ባይሆን ህወሃት አድጎና ጎልምሶ በእርጅናዬም ከጎጥ በረቴ አልወጣም ብሎ የሙጥኝ ካለ ነው ወቀሳውም፣ ነቀፌታውም፣ የታሪክ ጠባሳውም እስከ ወዲያኛው ይዞት የሚዘልቀው፡፡ በእርግጥ የአክሱምን መንበርና የአፄ ዮሐንስ አራተኛን አልጋ ከሰሜን ተነቅሎ ሸዋ መዝረጋቱ ቁጭት ሊፈጥር ይችል ይሆናል፡፡ አፄ ምኒሊክ መረብ ምላሽን ለጣልያን አስረክበው ትግርኛ ተናጋሪውን ኃይል ለሁለት ገምሰው አዳከሙት የሚለውን ትርክት ሲሰማ ያደገ ትውልድ ቁጭት ሊኖረው ይችል ይሆናል፡፡ በታሪክ አጋጣሚም ሆነ በልሂቃኑ ርብርብ አማርኛ ባህልና ቋንቋ በሌሎች ባህሎችና ቋንቋዎች ኪሳራ የተቆናጠጠው የአገሪቱ የማንነት መገለጫ እሴታዊ መንበር አሁንም ቁጭት ፈጥሮ ሊሆን ይችላል፡፡ በተፈጥሮ አቀማመጥም ሆነ በአፄ ኃ/ሥላሴ ዘመን በነበረው የፊውዳል ኢኮኖሚ ስርዓተ ትድድር ትግራይን የድርቅ፣ የችግርና የችጋር መገለጫ ተደርጎ እስከመወሰድ ያደረሱት ክስቶተች ከቁጭት አልፈው ትውልዱን አንገብግበውት ይሆናል፡፡ አልፎ ተርፎም በ15ኛው ክ/ዘመን በክርስትና እምነት አስተምህሮ የአስተሳሰብ ልዩነት የተነሳ አይናቸው ተጎልጉሎ ምላሳቸው ተቆርጦ የተፈጁት የትግራዩ የአባ እስጢፋኖስ ተከታዮች እልቂት ለ”እኛና እነሱ” ተቧድኖ በእርሾነት አገልግሎ በአማራው ገዥ መደብና ከቤተ መንግስቱ ጋር ጋብቻ ተፈጣጥሞ ከነበረው ቤተ ክህነት ጋር ከማቃረንም አልፎ ቁጭትና ብሶትን ፈጥሮ ሊሆን ይችላል፡፡ ከተጠራቀመው ብሶትና ቁጭትም ሆነ በጣልያን ግማሽ ምዕተ አመት የኤርትራ የቅኝ ግዛት ውጤት ምክንያት በርከት ያሉ ትግርኛ ተናጋሪዎች (ከሌላ ብሔሮች ንፅፅራዊ ጥናት ተደርጎ ቁልጭ ያለ የቁጥር ስዕል ማየት ባንችልም ቅሉ) በጣልያን ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ዘመቻና የቀኝ ግዛት አስተዳደር ውስጥ በመካተታቸው ትግራውያኑን በባንዳነት መፈረጃቸው ቅሬታንና ባይተዋርነትን ፈጥሮም ሊሆን ይችላል፡፡ በንጉሱም ሆነ በወታደራዊ አስተዳደር ዘመን የውስጥ ችግርን ትክክለኛ መንስኤ ተረድቶ መፍትሔ ካለማፈላለግ የተነሳ በተሸነቆሩት ቀዳዳዎች ሁሉ የውጭ ኃይላት ከላይ የተዘረዘሩትን ቁጭቶችና ብሶቶች ተጠቅመውበት የያኔውን የትግራይ ወጣቶች በእጅ አዙር ኢትዮጵያን ለማዳከም እንደ መሳሪያ ተጠቀሙባቸውም ሊሆን ይችላል፡፡ ከላይ በጠቃቀስናቸው ድምር ምክንያቶችም ሆነ እዚህ ባልተነካኩ ሌሎች ምክንያቶች የትግራይ ወጣቶች ብረት አንሱ፣ እልህ አስጨራሽ ትግልን ተጋፈጡ፡፡ ቢያንስ ለ 17 ዓመታት በጽናት ዱር ቤቴ ብለው በረሃ ቆዩ፡፡ በዚህም መካከል የታላቋ ሶቭየት ህብረት መፍረክረክ እሙን ሆነ፣ ደርግ ቀኝ እጁን አጣ፡፡ ተዳከመም፡፡ ህውሃት ሳይታሰብ በለስ ይቀናው ጀመር፡፡ ለዓመታት ያልታዩ ድሎችን በወራት መጎናጸፍ ጀመረ፡፡ ለትንሹ ቤት ሲተጋ ትልቁ ቤት በርገድ ብሎ መከፈቱን ተመለከተ፡፡ ህውሃት ጊዜ አላጠፋም፡፡ በአገሪቷም እዚህም እዛም ቦግ ቦግ ይል የነበረው የማንነት ጥያቄዎች ጠልፎና በደንብ አራግቦ ከወዶ ገቡም፣ ከምርኮኛውም ሰብሰብ ሰብሰብ አድርጎ አሻንጉሊት የብሔር ድርጅቶችን ፈጠረ፡፡ ወደ ሸገርም ገሰገሰ፡፡ ይህንን ክስተት አንዳንዶች እድል ይሉታል፡፡ ምናልባትም የህወሃት አጋጣሚን የመጠቀም ችሎታ ተደርጎ ቢቆጠርለት ክፋት የለውም፡፡ 3 ህወሃት ደጋግሞ እንደሚገልፀው ትግራውያንን የማያሳትፍ የአንድ ብሔር ፖለቲካዊ ፣ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ የበላይነትን በአንድነት ካባ ስር የተንሰራፋበት ኢትዮጵያ ጋር ተጠብቆ ከመኖር ኢትዮጵያዊነትን አውልቆ መጣል ሳይሻል አይቀርም አይነቱን የትግል መቀስቀሻ ህሳቤዎች ኤርትራን እንዳስገነጠሏት ሌሎቹንም የማንነት ጥያቄ አንጋቢዎች ወደ መገንጠል፣ አገሪቷንም ወደ መበታተን ማድረሱ አይቀሬ ነበር ነው የህውሃቶች ዋነኛ መከራከሪያ ነጥብ፡፡ ዳሩ ግን በአንድነት ስም ሌሎችን ጨፍላቂ የሆነውን አገዛዝ ከአዶ ሸገር ማስወገድ ከተቻለማ የምን መገንጠል ? ያሉ ይመስላሉ ህውሃቶች፡፡ ከመገንጠል አገሪቷን አፍርሶ መገንባት ሳይሻል አይቀርም ነው የህወሃት አመክንዮ፡፡ የአማራውን ገዢ መደብ እና በኦርቶዶክስ ቤተ ክህነት ስር ከጠረነፋቸው የሌላ ብሔር ተለጣፊዎች ጋር በጥቅል ማዳከም እንዲሁም የጭቆና ቀንበር ለዘመናት ተሸከምኩ ፣ ጎበጥኩኝ የሚለውን ሰፊውን የኦሮሞ ህዝብንና ሌሎችን በብሔርና በሃይማኖት ማንነታቸው ዳር ዳር ተገፍተው ተገልለው የነበሩ ብሔሮችን በፌዴራሊዝሙ እንጥፍጣፊ ለጊዜው እንዲፈነጥዙ መልቀቅ፡፡ ትግራውያኑን በሁሉ ጠቅልል ፖሊሲ ትግበራ መሰረት ወደላቀ ደረጃ ማሸጋገር፡፡ ይህ ነው ህወሃት ከ1981 ወዲህ ከአላማጣ አላልፍም ብሎ የነበረውን ካድሬና ታጋይ የማሳመን ስራ ከሰራ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ያደረገው ግስጋሴ ቀመር፡፡ በዚህ መሰረት ህወሃት አገሪቷ በኢህአዴግ ስም ከተቋጣጠረ በኋላ ያሉትን ቁጭቶች ለመሻርም ሆነ ዳግም ወደ ቁልቁለት ላለመውረድ ኮስተር ያለ ስትራቴጂ ለመንደፍ እንደሚግተረተር እሙን ነው፡፡ ዋናው ግብ የተደራጀ፣ የነቃ በማንኛውም ዘርፍ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሊሆን የሚችል የትግራይ ልሂቃንን በማፍራት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ቀንድ አካባቢዎች ወሳኝ የሆነ ማህበረሰብ የመፍጠርን ሩጫ ተያይዞታል፡፡ ይህንንም ለመተግበር የትግራይ ህዝብ ካለው የህዝብ ብዛት አንፃር አዳጋች ስለሚሆን የተለያዩ ንዑስ ስትራቴጂዎች መንደፋቸው የግድ ይላል፡፡ ለምሳሌ የመንግስት መ/ቤቶችና የልማታዊ ድርጅቶች መዋቅርን መቆጣጠር፣መከላከያና ደህንነት ተቋማትን ሙሉ በሙሉ መዘወር በሚያስችል መልኩ መቆጣጠር፣በአጭር ጊዜ ባለ ኃብት የመፍጠር ትልም፣ የተማረ የሰው ኃይል የማምረትና ወሣኝ የአገሪቷን የስልጣን ተዋረዶች ያለምንም ይሉኝታ ከወረዳ እስከ ሚኒስቴር መ/ቤቶች ድረስ፣ ከስፖርት ኮሚቴዎች እስከ ፍትህ አካላት አመራር መንበሮችን መጨበጥና በንግዱም ከጥቃቅንና አነስተኛ እስከ ኢንዱስትሪ ግንባታ ቅርምት በትጋት ሩጫውን የተያያዙት፡፡ አልፎ ተርፎም ተፅዕኖ ፈጣሪ ዲያስፖራ ለማፍራት በአሜሪካና በአውሮፓ አገራት መንጎዳጎዱን በሰፊው የገፉበት፡፡ የትግራይ መልካ ምድራዊ ጠርዞቾን መለጠጡም አጎራባች ክልሎችን ጂኦ ስትራቴጂያዊ ግዛቶቻቸውን ከማሳጣቱም በተጨማሪ ትግራይ የለም መሬትና በምዕራብና በምስራቅ አዋሳኞቹ ከባህር በር ባለቤት ጎረቤት አገራት ጋር ኩታ ገጠም የማድረግ ርብርቡም የዚህ ሁሉ ጠቅል አባዜ ንዑስ ስትራቴጂ ትግበራ ውስጥ የሚካተት ነው፡፡ ይህንን ስትራቴጂ ለማስፈፀም አገሪቷ ካላት ውስን ሃብት መቀራመት የግድ ስለሚል በሌላው ህዝብ ኪሳራ ህወሃት አላማውን ለመተግበር ላይ ታች ኳትኗል፡፡ ይህ ተፅዕኖ ፈጣሪ ልሂቅ የመፍጠር ረጅም የጉዞ ሂደት ውስጥ ሁሉን ጠቅልል የሆነ ኃይል መጨበጡ የግድ እንደሚል ህወሃት አላጣውም፡፡ ይህንን ሁሉን ጠቅል የሆነ ኃይል ግን ለዘመናት መያዙ አንኳን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ብዙ ብሔሮችና የተለያዩ ማንነቶች ባሉባት 4 ሀገር እና በትግራይ ህዝብ የቁጥር ድርሻ አንፃር ብቻም ሳይሆን በታሪክም በየትኛውም አካባቢ ዘላለማዊ ፈላጭ ቆራጭነት ባለመኖሩ ህወሃት ስትራቴጂውን መተግበሪያ የጊዜ እቅድ ሊኖረው እንደሚችል ጥርጥር አይኖረውም፡፡ 50ም ሆነ 60 ዓመታት የሚፈጅ ሁሉን ጠቅልል የኃይል አሰላለፍ ሚዛንን ማስጠበቅ፡፡ ግማሹ ሂደት በድል የተጠናቀቀ ይመስላል ቀሪው ግን ብዙ አደናቃፊ ተግዳሮቶች የሚደቀኑበት መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ በተጠበቁም ሆነ ባልተጠበቁ ተግዳሮቶች፡፡ ህወሃት ለ 50 እና 60 ዓመታት ኢህአዴግን እየዘወረ የትግራውያንን በሁሉም ዘርፍ ቆጥ ቆጡን የማቆናጠጥ ተልዕኮ ከተሣካ በኋላ ድርጅቱን አይዲዮሎጂ ተኮር ህብረ ብሔራዊ ቅርፅ በማላበስ የአገሪቷን ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ አወቃቀርንም ቋንቋን ብቻ መሰረት ካደረገ አደረጃጀት በማላቀቅ ጂኦግራፊያዊ ቅርርብን፣የኢኮኖሚ የባህልና ታሪካዊ መስተጋብሮችን ባማከለ መልኩ የመለወጥ ትልም አንግቦ እየተንቀሳቀሰ ይሆናል ብለው የሚጠረጥሩ አልጠፉም፡፡ በዚህ መካከል ሌሎች ክልሎችም በመርህ ደረጃ በተፈቀደላቸውና በተግባር በሚያገኙት ሽንቁር የምታህል እድል ተጠቅመው ህዝባቸውን በአገሪቷ ፖለቲኮ ኢኮኖሚና በማህበራዊ የእሴት እርከኖች ድርሻቸውን ከፍ ማድረግ ከቻሉ ለጌቶች ሲዘንብ ለሌላው ያንጠባጥባል አይነቱ እምርታ ቢሆንም ባልከፋ ነበር፡፡ ካልሆነም ፊሽካው ሲነፋ ሁሉም ሊቀያየር የተተለመ ይመስላል ባዮች በርካቶች ናቸው፡፡ ያም ሆነ ይህ ህወሃት ይህንን እቅድ አንግቦ ከተጓዘም ለአገሪቷ አለመበታተን መድህን የመሆን የፕሮፖጋንዳ ፍጆታ በዘለለ መልኩ በቁጥር ህዳጣን የሆነውን የትግራይ ህዝብና ልሂቃን ከተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ የበቀል በትር ሊታደግ የሚችልበት ብቸኛ ዋስትና ይህና ይህ ብቻ በመሆኑ ነው፡፡ በሂደት የብሔር ካርድን ወደ አቧራማው መደርደሪያ መሸጎጥ ፣ ህብረ ብሔራዊነትን ማቀንቀን፡፡ ዳሩ ግን የህወሃትን ሁሉን ጠቅል ጉዞ ከሚግደረደሩት ኩነቶች መካከል የዚህ ፅንስ ሀሳብ ፈጣሪና ዋነኛ አቀንቃኝ የነበሩት ታጋይ መለስ ዜናዊ ህልፈተ ህይወት አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር የቀመሩ ፈላስፋ እንደመሆናቸው አፈፃፀሙንም ከእርሳቸው የተሻለ ሊተገብር የሚችል ብቁ የሆነ አመራር ህወሃት ያላት አትመስልም፡፡ ብቃቱ የጭንቅላት ብስለትና ብልጠት ብቻም ሳይሆን ታጋይ መለስ የተጎናፀፉት ከጫካ እስከ ከተማ አብሯቸው የሚግተለተሉት የመከላከያና የደህንነት መዋቅር መረብ ማንም ተተኪ በቀላሉ ሊቆጣጠረው በማይችል መልኩ የተቀየሱ በመሆናቸውም ጭምር ነው፡፡ ሰውየውም በማኪቬላዊ አስተምህሮት መሰረት ብቃት ያለው ተተኪ አለማፍራታቸውም ሆነ ከአጠገባቸው አለማቅረባቸው ለህወሃት ትተውለት የሄዱት እዳ መሆኑ አይካድም፡፡ ከእሳቸው ሞት በኋላ በህወሃት መካከል ብቻም ሳይሆን በተቀሩት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል የታየው አንፃራዊ ድፍረት ህወሃት ኢህአዴግን የሚዘውርበት ጡንቻው በመጠኑም ቢሆን መላላቱ በግልፅ የሚታይ ኩነት ሆኗል፡፡ ሌላኛው የህወሃትን የአባ ጠቅል ረጅም ጉዞ ተግደርዳሪ ክስተት ታክቲካል የሆነው የአማራና የኦሮሞ የህዝብ ትግል አጋርነት ጅማሮ ነው፡፡ ምንም እንኳን የሁለቱም ወገኖች የፖለቲካ አመራርና ልሂቃን ህወሃት ካስቀመጠላቸው ወጥመድ ወጥተው አንዱ የሌላኛውን እውነታ ላለመመልከት በጨለማ ግርዶሽ ተውጠው ላለፉት 25 ዓመታት ለህወሃት ትልሙን የማስፈፀሚያ እፎይታ ጊዜ ቢሰጡትም ቅሉ በመሬት ያለው ህዝብ ግን ቢያንስ ቢያንስ የጋራ አውዳሚ የሆነውን ትልም የማኮላሸት አላማ ባነገበ መልኩ የጀመረው ህዝባዊ እምቢተኝነት ህወሃት ከባቡር ሃዲዱ ወረድ ብሎ ደግሞ ደጋግሞ እንዲያስብ የሚያስገድደው ተግዳሮት 5 መሆኑ እሙን ነው፡፡ ከእነዚህ ሁለት አበይት ተግዳሮቶች በመንደርደር ኢህአዴግ በምንም መልኩ የቀድሞ የህወሃት አሻንጉሊት ሆኖ ሊቀጥል ወደማይችልበት ደረጃ መሸጋገሩን መገመት አይከብድም፡፡ ግዑዝ አካል እንጂ ማንም ህይወት ያለው ፍጡር ከእነዚህ ሁለት አንኳር አስፈንጣሪ ግፊቶች በኋላ መልኩና ይዘቱን አይለውጥም ብሎ መገመት የሚያዳግት ይመስላል፡፡ ህወሃት የጀመርኩትን የሀዲድ መስመር ለቅቄ አልወርድም ካለ አገሪቷን መበተን ብቻም ሳይሆን መሰረቴ የሚለውን የትግራይ ህዝብንም ከከባድ እልቂት ለመታደግ እንደሚያዳግተው ከወዲሁ የተገነዘበ ይመስላል፡፡ በመሆኑም ብቸኛ አማራጩ ላለፉት 25 ዓመታት ያካበተውን አእምሮአዊ እና ቁሳዊ ሃብት ተመስገን ብሎ በማጣጣም ቀሪውን ጊዜ ከሌሎች የኢህአዴግ ድርጅቶች ጋር ተመጣጣኝ በሆነ የወሳኝነት ሚና ራሱን ገድቦ በሂደትም ድርጅቶቹን ርዕዮተ ዓለም ላይ የተመረኮዘ ህብረ ብሔራዊ ቅርፅ እያላበሰ መሄድ የግድ የሚል ይሆናል፡፡ ይህ ሂደት ድህረ ታጋይ መለስ ህልፈት እንደተመለከትነው የአገሪቷ የፖለቲካ ስልጣን የህወሃት ከሌሎቹ አባል ድርጅቶች ጋር ተካፍሎ እየመራ እንደመሆኑ በቀጣይ የኢህአዴግ የለውጥ ሂደት ደግሞ የመከላከያና የደህንነት ተቋማት ድርሻውንም ተመጣጣኝ ማድረግ እንዲሁም የሲቪል ሰርቪሱን ከፍ ሲል ሙያና ብቃትን መሰረት ባደረገ ቢያንስ ደግሞ ሁሉም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ተመጣጣኝ ድርሻ እንዲኖራቸው ማድረጉ አስገዳጅ ይመስላል፡፡ ይህ የኢህአዴግ የውስጥ ለውጥ ለቀጣይ የዴሞክራሲ እድገትና ቱርፋቶች በር ከፋች ብቸኛ መንገድ ይሆናል፡፡ ፍጥረታት ሙሉ ልውጠተ ቅርፅ ለማገባደድ የግድ ማለፍ እንደሚገባቸው egg – larva – Pupa – Adult የሚባሉት ደረጃዎች ሁሉ ኢትዮጵያም አሁን ባለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንፃር አይቀሬ የሚባሉ እርከኖችን ዘላ በህዝብ እንቢተኝነትና አመፁ ብቻ በቀጥታ ወደ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር መግባቱ አዳጋችና የማይታሰብ እንደሚሆንባት ማመኑ የግድ ይላል፡፡ አገሪቷ አሁን ባለችበት የዲሞክራሲ እድገት ደረጃ ሰላማዊውም ሆነ ሌላው አይነት ትግል ለለውጡ አጋዥ ኃይል ከመሆን ያለፈ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል ብሎ መከራከር ጉንጭ አለፍ ከመሆን አይዘልም፡፡ በእርግጥ አገራችን ወደ ዴሞክራሲያዊ ቱርፋት ለመዝለቅ ይህን ያክል ረጅም ጉዞ ለምን አስፈለጋት ብሎ መቆጨትና መንገብገብም ማንም ሊረዳው የሚችል መሆኑ ባይከብድም ጊዜ ወሳጅ መሆኑን መገንዘብ ግን ግድ የሚል ይመስላል፡፡ እርግጥ ነው ብዙ አቋራጭ መንገዶች ተዘግተውብን በረጅሙ መንገድ መንጓተታችን አይካድም፡፡ የሩቁን እንኳን ትተን ምናልባትም ንጉሱ ወራሽ አግኝተው የፊውዳል ትድድሩን ወደ Constitutional Monarchy እና ኢኮኖሚውን ከፊዳላዊ ቀንበር አላቀውት ቢሆን ኖሮ ህዝባችን የተራዘመ የኮሚኒዝም ስርዓት ገፈት ቀማሽ ባልሆነ ነበር፡፡ ከዚያም አልፎ ደርግ በአገሪቷ በየአቅጣጫው የተነሱትን የማንነት ጥያቄዎች እራሱ ባቋቋመው የብሄረሰብ ጥናት ኢንስቲትዩት ሙህራን ካቀረቡለት አማራጮች በአንድነት ጥላ ስር የማንነት ጥያቄዎችን መመለስ ቢቻል ኖሮ ህወሃት ጠልፎ የሚያጮኸው አጀንዳ ሊያጣ ይችል ነበር፡፡ ይህ ቢሆን አገሪቷ ላለፉት 25 ዓመታት ያየችውን የአንድ ብሔር የሁሉ ጠቅል ፖሊሲ ትግበራ ያልተወራረደ ሂሳብ ባልተሸከመች ነበር፡፡ እንደዚህ እንደዚህ እያልን ማለቂያ ወደሌለው ቢሆን ኖሮዎች ውስጥ ከመዘፈቅ ወሳኙ ነገር አሁን ካለንበት ነባራዊ ሁኔታ አንፃር በየትኛው ሂደት መታለፍ እንዳለበት መመራመር 6 ለተግባራዊነቱም ከታክቲካል ወዳጅነት ያለፍ ስትራቴጂያዊ ውህደቶችን መፍጠሩ የግድ የሚል ይመስላል፡፡ ኢህአዴግ ከእንግዲህ የቀድሞ ኢህአዴግ እንደማይሆን ጥርጥር የለውም፡፡ ኢህአዴግ ይለወጣል ወይም ይፈርሳል፡፡ አገሪቷ አሁን በያዘችው የፖለቲካ ቅርፅ ኢህአዴግ መፍረሱ ለህልውናዋ አደጋ ነው ከተባለ ትክክለኛ የእድገት እርከኖችን ጠብቆ ኢህአዴግ መለወጥ ይኖርበታል፡፡ ሲጀመር አራቱ ድርጅቶች ተመጣጣኝ ስልጣን በፖለቲካ፣ መከላከያ፣ ደህንነትና የኢኮኖሚ አውታሮች ውስጥ ሊቀዳጁ ይገባል፡፡ በመቀጠልም ኢህአዴግ አይዲዮሎጂ ተኮር ህበረ ብሔር ሊሆን የግድ ይለዋል፡፡ ዛሬ ፌዴራሊዝሙ መጣላችሁ የተባሉ ጋምቤላ ይሁን ሱማሌ ፣ አፋር ይሁን ሐረሪ የኢህአዴግ አባል ሊሆኑ ባለመቻላቸው ብቻ ምንም እንኳን አገሪቷን የመምራት ብቃት ቢኖራቸውም ከማህበራዊ ጉዳዮች ፣ ባህልና ቱሪዝምና መሰል የሚኒስቴር መ/ቤቶች የዘለለ ወሳኝ የፖለቲካ ቢሮዎች ጋር መጠጋት አይቻላቸውም፡፡ ይህ በንጉሱም ሆነ በደርግ ስርዓት ያልታየ ግልጽ የሁለተኛ ዜግነት ኢፍትሃዊ ጭቆና ነው፡፡ እነዚህ በተለምዶ አጋር የተባሉት ከኢህአዴግ አባልነት የተገፉ ብሔሮች ከዚህ በላይ ሊጨቆኑ የሚችሉበት መሳሪያ የለም፡፡ በገዛ አገራቸው በባህል ሙዚቃዎቻቸው ከመጨፈርና ከመዝለል ያላለፉ ባይተዋሮችና የበይ ተመልካቾች ተደርገዋል፡፡ ኢህአዴግ በአባል ድርጅቶች መካከልም ሆነ ከአጋሮቹ ጋር ባለው ጤናማ ያልሆነ ስርዓተ ትድድር ከዚህ በላይ መቀጠል ስለማይኖርበት ብቻም ሳይሆን ስለማይችል ወደ ህብረ ብሔራዊ ድርጅት ከተለወጠ የመከላከያና የደህንነት መዋቅሮች ጭምር አብረው ይለወጣሉ፡፡ ያኔ ነው የህዝብ እምቢተኝነትና አመፅ ቀጥተኛ ተፅዕኖ መንግሥት ላይ ማሳረፍ የሚቻላቸው፡፡ አንድን አምባገነን ስርዓት ለመጣል በስርዓቱ ያኮረፈ ወሣኝ ቦታዎችን የተቆናጠጠ ባለስልጣን ፣ የጦር መሪ ፣ የደህንነት መዋቅር እንዲሁም ወገኔ ላይ አልተኩስም የሚል ህብረ ብሔር ጦር የግድ ይላል፡፡ በመሆኑም የሰሞኑ ትኩሳቶች ተጠናክረውና ተደራጅተው ኢህአዴግን መልክና ይዘቱን እንዲለውጥ ማስገደድ ይኖርባቸዋል፡፡ ትግሉን በተቀናጀና በተደራጀ መልኩ መምራትና ከአጉል ተስፈኝነት የዘለለ ምክንያታዊና እርከናዊ ውጤቶችን አልሞ መጓዙን ከልሂቃኑ የሚጠበቅ ብቻም ሳይሆን ጊዜው የሚጠይቀው ወሳኝ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ከማይጨበጥ ህልም ዓለም ተወጥቶ መሬት ላይ ካለው እውነታ ጋር መታረቁ በኢህአዴግም ሆነ በተቃዋሚው ጎራ ላሉት ቡድኖች አማራጭ የለሽ መሆኑን በፅኑ መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ ኢህአዴግ እራሱን ከጎጥ አስተሳሰብ አላቆ ወደ ህብረ ብሔራዊና ርዕዮተ ዓለማዊ ፓርቲነት እስካለወጠ ድረስ አደጋው ለአገሪቷ ህልውና ብቻም አይደለም፡፡ ዛሬ በየክልሉ የሚገኙ ገዢ መደቦች እና በመከላከያ ተቋማት ውስጥ የተፈጠሩት ማፍያ መሰል ቡድኖች ነገ የወለዳቸውን ድርጅት ተብትበው ላለመጣላቸው እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ ባቄላዋ ስትከርም ባረጀው የኢህአዴግ ጥርስ አለመታኘኳ እሙን ነውና፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የተቃዋሚ ጎራውም ኢህአዴግን ከማስወገድ የዘለለ ጥልቀት ያለው የአስተሳሰብ እምርታ ማድረግን ግድ የሚል ይመስላል፡፡ በምኒሊክ ጊዜ የደነቆረ አይነት እንዳይሆን ራሳቸውን መሬት ላይ ካለው ከተጨባጩ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ማላመዱን ከወዲሁ ቢያያዙት ይመረጣል፡፡ በአገሪቷ ህዝቦች መካከል ያሉት የማያግባቡ የታሪክም ሆነ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የአስተሳሰብ ልዩነቶች በጥልቀት እያጠኑ፣ እየተወያዩ የድርጅታቸውንም ሆነ የአመራር ልሂቃኑን አመለካከቶች ወደ መሐል መንገድ ማሸጋገርና 7 ማቀራረብ እጅግ ወሳኝ ነጥብ ሆኗል፡፡ በሁሉም አቅጣጫዎች ይህን መሰል እርከናዊ እርምጃዎችን መኬድ ካልተቻለ የሰሞኑ እንቅስቃሴ እንደከዚህ ቀደሞቹ የህዝብ መሪዎችን፣ ወጣቱን እናም ሚዛን አጋደለ ብሎ ከህቡ ይፋ የሚወጡትን ዜጎች በአዞ አስበልቶ ተመላሽ ሽንቁር ጀልባ እንዳይሆን መጠንቀቁ ሳይበጅ አይቀርም፡፡ አዲሱ ዓመት በሁሉም አቅጣጫ እርከናዊ ሽግግር ጅማሮ ይሆንልን ዘንድ እንትጋ ! እንታገልም! መቼም እንፀልይ ብዬ አልቀልድምና፡፡ ራሚደስ ጷጉሜ 5 ቀን 2008 ዓ.ም